(ጅማ፣ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
ኢትዮጵያ በጅማ ከተማ የምታስተናግደው የዘንድሮው አለም አቀፍ የንብ ቀን እና 2ኛው የንብ ሀብት ልማት ፎረም በይፋ ተጀምሯል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀው የሌማት ትሩፋትን፣ አረንጓዴ አሻራን እና የስንዴ ልማትን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የንብ ቀን እና 2ኛው የንብ ሀብት ልማት ፎረምን ለማስተናገድ ዕድሉን በማግኘቷ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለንብ ሃብት ልማት ምቹ ስነ-ምህዳር እንዳላት የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ከ10 ሚሊየን በላይ ህብረ ንብም እንዳላት ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ አበበ ሃይለ ገብርኤል አለም አቀፍ የንብ ቀን የሚከበርበትን ዓላማ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ሁሉ ለንብ ሃብት ልማት ትኩረት እንዲሰጡና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ጋር በመተባበር የምታስናግደው አለም አቀፍ የንብ ቀን እና 2ኛው የንብ ሀብት ልማት ፎረም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 14/2017 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ሁነቶች በጅማ ከተማ ይካሄዳል፡፡
ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው