የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ በፊት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ምክኒያት ሀገራችን ባላት የእንስሳት ቁጥር ልክ ሳንጠቀም ቄይተናል፡፡ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ግን ለእንስሳት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት በተለይም ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በይፋ ከተጀመረ ወዲህ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ሀገራዊ ፕሮግራሞችን (ኢኒሼቲቮችን) ቀርፆ ተጫባጭ ውጤቶችን ካስመዘገበባቸው መካከል ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ የተጀመረ ሲሆን በአራት ዓመት (2015-2018 በጀት ዓመት) የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማህበረሰብ ውስጥ የማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የእንስሳት ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት፣ ኤክስፖርትን በማበረታታት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ እና የስራ ዕድል የመፍጠር ግቦችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የዚህም ፕሮግራም አላማ፡ የወተት፣ የዶሮና የማር፣ የዓሳና የቀይ ስጋ ምርቶችን ማሳደግ ሲሆን ለዓብነትም በአራቱ አመታት ውስጥ የላም ወተት ምርትን በ2014 ዓ.ም ከነበረበት ከ5.8 ወደ 10.3 ቢሊዮን ሊትር፣ የዶሮ እንቁላል ምርትን ከ3.2 ወደ 9.1 ቢሊየን እንቁላል፣ የዶሮ ስጋ ምርትን ከ90 ሺህ ወደ 240 ሺህ ቶን፣ የማር ምርትን ከ 147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ቶን ማድረስ ዝርዝር ዓላማዎቹ ናቸው፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ብቁ የሰው ሃይል የማፍራትና አገልግሎትን ለአርሶ/አርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በዓለም ባንክ ፕሮጀክት በጀት ድጋፍ በሆሎታ ከተማ የሚገነባውን ብሔራዊ ሁለገብ የወተት ልማት ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታን በይፋ ስራ ባስጀመሩበት ጊዜ፣ ከምርት አንፃር የሌማት ትሩፋት የ4 ዓመት ዕቅድን በ2 ዓመት ስላሳካን እቅዱን ከልሰን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ የእያንዳንዱን ቤት ገብቶ ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን ከተማና ገጠር ሳይል ሁሉም ባለችው ትንሽ ቦታ ላይ መስራት የሚችል ስራ ሆኗል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ እንደገለፁት ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ሲጀመር በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል አቅም እንደ ሀገር ግማሽ ሚሊየን ነበር፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን የማዳቀል አቅምን 3 ሚሊየን ማድረስ የተቻለ ሲሆን ባለፉት 8 ወራት ብቻ ቢያንስ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን የተሻሻሉ ጥጆች ተወልደዋል፡፡
አዳቃይ ቴክኒሺያኖችን በማሰልጠን ወደ ታች ወርደው ለአርሶ/አርብቶ አደሩ አገልግሎቱን እንዲሰጡ በማድረግም ይህ ውጤት ተገኝቷል፤ በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ ቃል ተገብቶ በይፋ የተጀመረው ሀገራዊ ሁለገብ የወተት ልማት ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታም እንደ ሀገር የሚፈለጉትን 20,000 አዳቃይ ቴክኒሺያኖችን በፍጥነት ማፍራት ያስችላል፡፡
በለውጡ መንግስት አንድ የመጣው የእይታ ለውጥ ችግሮችን ወደ እድል መቀየር ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ በፊት የነበረው የፈሳሽ ናይትሮጂን (Liquid Nitrogen) ማዕከል በጣም አርጅቶ በየጊዜ ስለሚበላሽ ችግር እንዳለ ጠቅሰው ዘንድሮ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ባለው 8 የፈሳሽ ናይትሮጂን ማዕከላት የፈሳሽ ናይትሮጂን አቅርቦት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ አስረድተዋል፡፡
በዶሮ ሀብት ልማት ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ሲጀመር እንደ ሀገር የሚሰራጨው የአንድ ቀን ጫጩት 26 ሚሊዮን ብቻ የነበረ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት 41 ሚሊዮን ማድረስ ተቻለ፡፡ ይህም በቂ አልነበረም፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ችግሩ ቅድመ-ውላጅ (Grand parent stock) የሚባለውን ከውጭ እንደሚያስመጣና እሱንም የውጭ ምንዛሪ (ፎሬክስ) ሲገኝ ብቻ እንደሚያመጣ ካሳወቀ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወዲያውኑ ሁኔታውን አመቻችተው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአመት መቶ ሚሊዮን ጫጩት የሚያመርት ግራንድ ፓረንት ስቶክ ማዕከልን በአንድ አመት ውስጥ መገንባት ተችሏል፡፡ በዚህም ዘንድሮ 150 ሚሊዮን ጫጩቶችን ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን በ8 ወር ወስጥ 85 ሚሊየን ጫጩቶችን ማሰራጨት ተችሏል፡፡
በሚኒስትሩ ገለፃ በማር ምርት በኩል በበጀት ዓመቱ በ8 ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 994 ዘመናዊ ቀፎዎች ተሰራጭተዋል፡፡ ዓሳን በሚመለከት በፊት ከሀይቆችና ከወንዞች ውስጥ አስግሮ መብላት ሲሆን አሁን አርሶአደሮች በጓሯቸው እንደ ዶሮና በግ በሰው ሰራሽ ኩሬዎች እንደፍላጎታቸው አርብተው በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ ባለፉት 8 ወራት ብቻ ወደ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የዓሳ ጫጩቶችን ማሰራጨት ተችሏል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም የሚሰራው ስራ ሁሉ በእውቀትና በቴክኖሎጂ መመራት እንዳለበት ጠቁመው፣ ይህንን አውን የሚያደርገው ብሔራዊ ሁለገብ የወተት ልማት ማሰልጠኛ ማዕከል ቴክኒሺያኖች ብቻ የሚሰለጥኑበት ሳይሆን ሞዴል አርሶ/አርብቶ አደሮችም ሰልጥነውበት ቴክኒሺያኖች የሚሆኑበት ይሆናል ብለዋል፡፡


በሆለታ የሚገኙ የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ልማት ማዕከሎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው በተለይ ከሆለታ ከተማ አስተዳደር ጋር ተቀናጅተው አብረው በማቀድ አብረው እንዲሰሩ ክቡር ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
#ከማምረትበላይ
#BeyondProduction
——————–
ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦
ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et
ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia
ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia
ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews