(ሰመራ፣ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
እንደ ሃገር ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት የስንዴ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ከሃገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
እነዚህንም አበረታች ውጤቶች ቀጣይነታቸውን ለማረጋገጥ እና ለማስፋፋት ግብርና ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክትን ተግባራዊ በማድረግ ወደ ስራ ተገብቷል።
በሃገር አቀፍ ደረጃም በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በመስኖ ማምረት ተግባራዊ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አንዱና ፋና ወጊው ሲሆን በዚህም ስንዴን በመስኖ በማምረት አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ክልሉ በሰብል ልማቱም እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ማሳየት ተችሏል።
በክልሉ ከሰባት ዓመታት በፊት በ22 ወረዳዎች ውስጥ የግብርና ልማት ስራዎች ሲከናወኑ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በ30 ወረዳዎች ላይ የግብርና ልማት ስራዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ በዋናነትም የአዋሽ ተፋሰስን ተከትሎ ባሉ አካባቢዎች ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመትም በሁሉም የሰብል አይነቶች ከ118 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት እንደተቻለ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
በክልሉ በግብርና ልማት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳዳግ እንዲያስችል የኢትዮጵያ የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ታሳቢ ያደረገ ውይይትና የመስክ ምልክታ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሄራዊ ማናጀር አቡድልሰመድ አብዶ በአፋር ክልል የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በዋናነትም በክልሉ በግብርና ልማት ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው፤ በአፋር ክልል የተጀመረው ስንዴን በመስኖ የማልማት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
ስራ አስፈጻሚው አያይዘውም የክልሉን ግብርና ምርታማነት በተለይም የሰብል ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሁም ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረጉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር:- ማቲዎስ ተገኝ