/ባህርዳር፣ መጋቢት 25፣ 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገቱ የተረጋገጠ እና ምርታማ የሆነ ትውልድ መፍጠር ወሳኝ ሚና አለው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጨመርና በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረገው ጎን ለጎን የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትና መጓደል ችግርን ለመቅረፍ የምግብ እና የስርዓተ-ምግብ መርሃ-ግብር ቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል።

የግብርና ሚኒስቴር የምግብ ብክነትን ከመቀነስ፣ ጥራትና ደህንነትን ከማስጠበቅ አንጻር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሄራዊ የምግብ ደህንነትና ጥራት፣ የድህረ ምርት አያያዝ እና የስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ይፋ ካደረገ በኋላ ከክልል ግብርና ቢሮዎችና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ስትራቴጂዎችን የማስተዋወቅ ስራ በየክልሎች እየሰራ ይገኛል፡፡
ስትራቴጂዎችን በአማራ ክልል ለመተግበር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የፌዴራልና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐሚድ ጀማል(ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ በምግብ ንጥረ ነገር የበለፀገ፣ ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ፣ የተሰባጠረና በቂ የምግብ አቅርቦት ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረው ስትራቴጂዎች አገሪቱ ለስርዓተ-ምግብ ደህንነትና ለምግብ ሉዓላዊነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግብርናው ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማነቱ እያደገና ኮሜርሻላይዝድ እየሆነ መምጣጡን ዶ/ር ሐሚድ ገልፀው ከማምረት ባለፈ የምናመርተው ምርት ብክነትን የቀነሰ፣ ጥራትና ደህንነቱን የጠበቀ እና ስርዓተ ምግብ ተኮር በማድረግ የሰለጠነ የአመጋገብ ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲቻል ስትራቴጂዎችን በየክልሎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ስትራቴጂውን እስከ ቀበሌና አርሶና አርብቶአደሩ ድረስ በማስተዋወቅ ለመተግበር የግንዛቤ ማስረፅ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ዶ/ር ሐሚድ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቁና የዳበረ ዜጋን መፍጠር መሆኑን እና በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለመሻገር የተቀረፁ ስትራቴጂዎች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የስርዓተ-ምግብ ግንባታ አገር ከመገንባት የማይተናነስ በመሆኑ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር ጉልህ ድርሻ እንዳለውና ለዚህ ደግሞ ስትራቴጂውን አውቆና ተረድቶ ወደ ታች ማውረድና መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከስትራቴጂዎች ማስተዋወቅ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምግብን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ/Food Based Dietary Guideline/ የቀረበ ሲሆን የምግብ አሰራር ሰርቶ ማሳያና ፎቶ ጋለሪ ምልከታ ተደርጓል፡፡
ዘጋቢ:- ተዋበ ጫኔ
ካሜራ:- ያሬድ አሰፋ