
(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በስፔን ሲቪያ እ.አ.አ ከጁን 30 እስከ ጁላይ 3 ቀን 2025 እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው አለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ ጎን ለጎን በGlobal Alliance Against Poverty and Hunger እ.አ.አ ጁን 30 ቀን 2025 በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ባደረጉት ተሳትፎ፣ የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል ሀሳቦችን እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መሰረት አድረጎ የተዘጋጀ መሆኑ፣ በመንግስትና በህዝቡ በባለቤትነት የተያዘ መሆኑና ከዚህም አንጻር በተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ይህ ኢኒሼቲቭ በሀገር ውስጥ ሀብት ላይ በመመስረት የሚተገበር ሲሆን ይሁን አንጂ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በምናደርጋቸው ትብብሮች ለዚህ ኢኒሼቲቭ ድጋፍ ማፈላልግ በስፋት በመተግበርና ድህነትን ለመቀነስ ብሎም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ኢኒሼቲቩን በተጨማሪ ኢንቨስትመንት በስፋት መተግበር እንደሚቻል በመግለጽ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሌሎች ሀገራት መልካም ተሞክሮ ለመማርም ዝግጁ መሆኗን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት Mr. Akinwumi Adesina በስብሰባው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ባለፉታ አመታት በሰራችው አመርቂ ስራ በስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ ራሷን መቻሏን መስክረው፣ በትኩረት ተገቢው አመራር እና ድጋፍ ከተደረገ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚቻል የኢትዮጵያ ስኬት ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አክለውም በኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት አንዱ የልማት መስክ የሆነውን የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ለመደገፍ ባንኩ 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመደገፍ መወሰኑን ገልጸዋል።