FDRE Ministry of Agriculture

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ  ክልል  በርካታ ውጤቶችን አስገኝቷል

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ  ክልል  በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት  በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ባለፉት ቅርብ አመታት የተሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃና የአርንጓዴ አሻራ  የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞችን በማካሄድ የተራቆቱ አከባቢዎች አገግመዋል፤ ምርትና ምርታማነትም ጨምሯል፤ የደረቁ ምንጮች  በቂ ውሃ ማፈለቅ ጀምረዋል እንዲሁም አርሶ አደሮች የመኖ ሣር በበቂው ለከብቶቻቸው ማግኘት ችለዋል፡፡

በደቡብ ምህራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ  የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዘርፍ ኋላፊ  ውብሸት ዘነበ  በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ስራ በመሰራቱ  በምርትና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሆ ጠቅሰው ለወጣቶችም የስራ እድል በስፋት እየተፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ዘንድሮ በክልሉ በ6ቱም ዞኖች የሚኖሩ የገጠር ቤተሰቦችን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ማህበረሰቡን በማነቃቃትና በማሳተፍ ነባርና አዳዲስ 1100 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተሰርቷል ብለዋል፡፡ 

ይህም ዘለቄታ ባለው መልኩ የግብርና ምርትትና ምርታማነትን የሚያሳድግ የበለጸገ ተፋሰስ ልማትን ለማረጋገጥ ያሥችላል ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ከ213 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት  እንደለማ ተናግረዋል፡፡ 

ኃላፊው አያይዘውም በአርንጓዴ አሻራ ልማት ስራ በ2017 በጀት ዓመት በስነ- አካላዊ የለማውን መሬት በስነ -ህይወታዊ ሥራ ለመሸፈን 235 ሚሊዮን የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የአግሮ ፎረስተሪ፣ የደንና ፍራፈሬ ቸግኞችን በማዘጋጀት ከ211 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ምህራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ዳይሬክተርና የካልም አስተባባሪ ተረፈ ማሞ በበኩላቸው  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተፋሰስ ልማት ስራውና የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነ ጠቅሰው በፊት በአሲዳማነት የተጠቁ አከባቢውችን በማልማት ማህበረሰቡን ወደ ምርታማነት እየቀየረ ነው ብለዋል፡፡

በከፋ ዞን በሽሾ እንዴ ወረዳ  ዳራ ቀበሌ አፋለች ንዑስ ተፋሰስ ተሳታፊ አርሶ አደር ዘውዲቱ የቦ እንደገለፁት በፊት መሬታቸው በጎርፍና በንፋስ አፈሩ ተሸርሽሮ በመወሰዱ ምርት አይሰጥም ነበር፡፡  ነገር ግን በተፋሰስ ሥራ መሬታቸው አገግሞ በመልማቱ ምርታማ መሆን ችሏል፡፡ ዛሬ   በማሳቸው ሙዝ ፣ ቡና  እና የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

አርሶ አደር መክቴ ታደሰ በከፋ ዞን ጊንቦ ወረዳ ህብረት ቀበሌ ናዋሪ ናቸው፡፡ የቡቄ ኮሾ ተፋሰስ ተሳታፊ በመሆን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተፋሰስ ስራ ይሰራሉ፡፡ በአሁን ግዜ በተፋሰስ ልማት ስራው አከባቢያቸው በማገገሙ በጣም ምርታማ መሆን ችለዋል፡፡ ህብረተሰቡ የተፋሰስ ስራን ባህሉ እንዳደረገና በፍቃደኝነት ወቅቱን ጠብቆ እየሰራ እንደሚገኝም አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡

በገዋታ ወረዳ የሰንበቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰለሞን አሊ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢኖ ተፋሰስ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የመኖ ሳር በበቂው አግኝተዋል፡፡ በዚህም ከብት በማርባትና በማድለብ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ

ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *