FDRE Ministry of Agriculture

የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምን ከግብ ለማድረስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው

(ወልቂጤ፣ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2014 ዓ.ም ተግባራዊ ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ ለእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፉም መነቃቃትን ፈጥሯል።

ይህንንም ሃገራዊ ኢኒሼቲቭ ከግብ ለማድረስ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት በእንስሳት ጤና፣ ልማት፣ ዝርያ ማሻሻል እና ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም በውልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ዝርያቸው ተሻሽሎ የተባዙ ጊደሮችን ለተጠቃሚ አርሶአደሮች የማስረከብ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በዚህም 22 የወተት ጊደሮችና 4 ለድለባ የሚሆኑ ኮርማዎችን ለአካባቢው ሞዴል አርሶአደሮች ያስረከበ ሲሆን ይህም ተግባር የምርምር ማዕከሉ በየአካባቢው የወተት መንደሮችን ለመመስረት ያነገበውን ግብ ለማሳካት የሚያግዝ ነው።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የእንስሣት ዘርፉን ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የእንስሳት ጤናን መጠበቅ እንዲሁም የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

የወትተ ምርታማነትንም ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ 12 ቢሊዮን ሊትር ወተት ለማምረት ታቅዶ እስካሁን 8 ቢሊዮን ሊትር ማምረት እንደተቻለም ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በዛሬው ዕለት በወልቂጤ አካባቢ ለሚገኙ አርሶአደሮች የተሰራጩ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችና ኮርማዎች፤ አርሶአደሮቹ በምርምር ማዕከሉ በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት ጠብቀውና ተንከባክበው በመያዝ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር ንጉሴ ደቻሳ እንደተናገሩት እንደሃገር በእንስሳት ሃብት ዘርፍ ትልቅ አቅም ቢኖርም ምርታማነት ላይ ግን ውስንነት ይታያል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የምርታማነት ውስንነትን ለመቅረፍ በእንስሣት እንክብካቤ እና በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የወተት ምርታማነትን ለማሳደግም ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችን አርሶአደሮች ተደራሽ የማድረግ ተግባራት እየተከናወነ ሰለመሆኑም አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊ እያሱ ተረፈ እንደተናገሩት በክልሉ የእንስሳት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ም/ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በሌማት ትሩፋት መርሃግብርም እንደ ክልል ተጨባጭ ለውጥ የታየባቸው ተግባራቶች እንደተከናውኑም ተናግረዋል።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የወተት ምርታማነትን ለማሻሻል በኢንስቲትዩቱ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከሌማት ትሩፋት መርሃግብር አንዱ ተግባር የወተት ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በመርሃግብሩ መጨረሻ ዓመት በ2018 ዓ.ም ምርቱን ወደ 17 ቢሊዮን ሊትር ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ም/አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው የጉራጌ ዞን በእንስሳት ሃብት ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ጊደሮችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግና ሃገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርን ለማሳካት አበርክቶው የላቀ ነው ብለዋል።

የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ሃበት ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ከእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት ጋር በትብብር የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ ለአርሶአደሮች እያስተላለፈ እንደሚገኝ በመርሃ-ግብሩ ተገልጿል።

ዝርያቸው ተሻሽሎ የተባዙ ጊደሮችን ካገኙ አርሶአደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አርሶአደር ቀድሩ ለማ፤ የተሰጣቸውን ጊደር በመንከባከብና በመጠበቅ የወተት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም በጉራጌ ዞን የሚገኙ አርሶአደሮች ተገኝተዋል፡፡

ከርክክብ መርሃ-ግብሩ ጎን ለጎንም የምርምር ማዕከሉ የተጎበኘ ሲሆን በምርምር ማዕከሉ በአየር ንብረት አፈፃፀም የመሬት አያያዝ ፕሮግራም (CALM) የበጀት ድጋፍ የተገነባ የአፈርና ውሃ ቤተ-ሙከራ በክብር እንግዶች ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፦ ማቲዎስ ተገኝ