FDRE Ministry of Agriculture

የንብ ሃብት ልማትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

የንብ ሃብት ልማትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

/ጅማ፣ የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

በግብርናው ዘርፍ የእንስሳት ሃብት ልማትን ምርታማነት በማሻሻል እያደገ የመጣውን የምግብና ስነ-ምግብ እንዲሁም ከአግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው  የምርት ፍላጎት ምርቱን በመጠንና በአይነት ለማሳደግ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ከዘርፉ የታሰበውን ምርታማነት ማሳካት ተችሏል፡፡

በዚህ ሂደት ያለውን ሰፊ ፀጋ በመጠቀም የባለድርሻ አካላትን ሚና ለማሳደግና የንቦችን ደህንነት በማስጠበቅ የሚፈለገውን ውጤት ለማሳካት ሰፊ ርብርብ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ ክልሉ በንብ ሃብት ልማት ሰፊ አቅምና ምቹ ስነ-ምህዳር ያለው ሲሆን እነዚህ ፀጋዎችን ለመጠቀም እንዲቻል ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ንቦች ለአጠቃላይ የግብርናው ሴክተር ምርትና ምርታማነት እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀው የማር ምርትና ውጤቶችን ከማበርከታቸው ባለፈ በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የርክበ-ብናኝ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የተፈጥሮ ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ክልሉ ያለውን ሰፊ የንብ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀም እያስቻለው መሆኑን እና በንብ ሃብት ልማት የመጣው ለውጥ አበረታች ቢሆንም ክልሉ ካለው ሰፊ አቅም አንጻር የማር ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ለኤክስፖርት የሚሆን የማር ምርትን በብዛት ማምረት እና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ላይ በታሰበው ልክ እንዲጓዝ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ ማስረሻ ተናግረዋል፡፡

የዘርፉ ተዋንያን ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የንብ ሃብቱን ለማሳደግ  ሁሉም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኃላፊው ገልጸው፣ የግብርና ሚኒስቴር እና አለም አቀፍ የስነ-ነፍሳት ሳይንስና ስነ-ምህዳር ማዕከል/ኢሲፔ/ የአስተባባሪነትና ድጋፍ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ንቦች ከሚሰጡት የማር ምርት ጠቀሜታ በተጨማሪ የሚሰጡትን የርክበ-ብናኝ እና ሌሎች አገልግሎቶች ማሳደግ ላይ በቅንጅት ለመስራት እንዲቻል ለክልሉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በጅማ ከተማ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ ግብርናው በሁሉም ዘርፍ ባስመዘገበው አበረታች ውጤት የምግብ ዋስትናና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ፈጣን ጉዞ ላይ መሆኑን ገልፀው በዚህ ሂደት የእንስሳት ዘርፉ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ እተሰሩ ካሉ ስራዎች አንዱ ማር መሆኑን እና በዚህም የንብ ሃብት ልማቱ በመነቃቃቱ ወጣቶች በዚህ ስራ ልዩ ተሳትፎ እያደረጉና ሰፊ የስራ እድል እያገኙ እንደሆነ አቶ ግርማ ገልፀው፣ በንብ ማነብ ስራ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ በመስራት የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማር ምርትና ምርታማነትን በአገር ደረጃ ለማሳደግ ፀጋዎቻችንን መጠቀም እንደሚገባና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምርትና ምርታማነትን ከምናሳካበቸው ክልሎች አንዱ መሆኑን አቶ ግርማ ጠቅሰው፣ ከማምረት ባለፈ የማር ጥራትን በማሳደግ በሁሉም ገበያ አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

በየክልሎች የሚመረቱ የማር አይነቶች የየራሳቸውን ብራንድ/መለያ/ በመያዝ እንዲመረቱ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉት ድጋፍ አበረታች መሆኑንም አማካሪው ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡-           ተዋበ ጫኔ

ፎቶግራፈር፡-      ዮዲት እንዳለው