FDRE Ministry of Agriculture

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምን ለውጥ አመጣ ?

የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ኘሮግራም እንደ ሀገር በድርቅ፣ ተከታታይነት ባለው  በዝናብ እጥረት፣ በእርሻ መሬት ጥበትና በምርት መቀነስ  ምክንያት የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር የተከሰተባቸው የገጠር አካባቢዎች ላይ በማተኮር የምግብ ክፍተትን በመሙላት የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ጥሪትን መገንባት ዓላማ አድርጎ ሲተገብር ቆይቷል፤ ዛሬም እየተገበረ ይገኛል፡፡ ፕሮግራሙ የተጠቃሚዎችን ኑሮ ከመቀየሩና የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው እንዲለሙ ካማድረጉም ባሻገር ማህበረሰቡ  ሰርቶ የማግኘት አስተሳሰብና የስራ ባህልን  እንዲያዳብር በማድረግም የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ፕሮግራሙ እነዚህን ለውጦች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም አምጥቷል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዘርፍ ተወካይ አቶ ሳሊህ ሳኒ እንደገለፁት በክልሉ ስር ለሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር መንፅኤ ከሆኑት መካከል ዋንኛው ድርቅ ሲሆን ፕሮግራሙ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራቱ አካባቢው እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል፡፡

ከማህበራዊ ዘርፍ አንፃር ጤና ኬላን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ውሃን እና መንገድን የማስፋፋት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ተወካዩ፣ በተለይ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የማህበረሰብ ኩሬ በመቆፈር ውሃን ማቆር፣ ምንጭን ማጎልበት፣ አነስተኛ የመጠጥ ውሃ ግንባታ እና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ስራዎችን ሰርቶ የማህበረሰቡን ችግሮች ማቃለሉን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ አማካኝነት ተጠቃሚዎችም ኑሯቸውን አሻሽለዋል፡፡ ሰርተው ከሚያገኙት እየቆጠቡ ጎን ለጎን በሚያገኙት ብድር የገቢ ማግኛ አማራጮችን በመፍጠር የቤተሰብ ጥሪት እንዲገነቡ ማድረግ ተችሏል፡፡ ሀብት አፍርተው መስፈርቶቹን በማሟላት የተመረቁ ተጠቃሚዎች በርካታ ናቸው፡፡

በክልሉ ውስጥ ያሉ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ብዛት 88,426 አባ/እማ ወራዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል የማህበረሰብ ስራ ሰርተው የሚደገፉ 73 ሺህ አባ/እማ ወራዎች ይሆናሉ፡፡ እንደ ሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሰርተው የሚደገፉ ተጠቃሚዎችን በሙሉ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል፣ አቶ ሳሊህ፡፡

ይህን ለማሳካት በፕሮግራሙ ድጋፍ ተጠቃሚዎች እንደፍላጎታቸው በፍራፍሬ፣ በቅመማቅመም፣ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ እንዲሁም በንግድ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ሳሊህ ገልፀዋል፡፡

በከንባታ ዞን የግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ሄሴቦ  በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ላይ ሰፊ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ተጠቃሚዎች የገጠር ገንዘብና ቁጠባ ህ/ሥ/ማህበር አባል ሆነው በመቆጠብ ተበድረው እንስሳት በማርባትና በማደለብ ሀብት አፍርተው ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ዶሮን በማርባት የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት ያለፈ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ገቢ ያገኛሉ ብለዋል፡፡

በፊት ያላቸውን አነስተኛ እርሻ መሬታቸውን አከራይተው የቀን ስራ የሚሰሩ አርሶ አደሮች  በፕሮግራሙ ከታቀፉ ወዲህ የስራ ባህላቸውንም በማሻሻል በላቸው እርሻ ማሳ ላይም በበልግ፣ በመኽር እና በበጋ ወቅቶች የተለያዩ ሰብሎችን በአግባቡ በማልማት ጥሩ ምርት ማግኘት እንደቻሉም  አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡

በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊና የአደጋ ስራ አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዮሐንስ ተጠቃሚዎች ከተረጂነት ወጥተው የምግብ ሉዓላዊነት እንዲያረጋግጡ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እስከ ቀበሌ ደረጃ በየመዋቅሩ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በተደጋጋሚ  መድረክ ተፈጥሮ  የግንዛቤ ማዳበሪያ ስራ በስፋት ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

ተጠቃሚዎችም ፕሮግራሙ ድንገት ሊቆም እንደሚችል መጠራጠር ጀምረዋል ያሉት ኃላፊው፣ ተረጂነት ውርደት መሆኑንም ተረድተው ድጋፉን በአግባቡ ተጠቅመው የራሳቸውን ጥረት ጨምረው ሁሉም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በቁርጠኝነት እየሰሩ ስለሆነ ከፕሮግራሙ ለመልቀቅም ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን አበራ  በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ የዛቶሾደራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በፊት ምንም ስላልነበራቸው በልቶ ለማደር እጅግ ይቸገሩ ነበር፤ የደሀ ደሀ ነበሩ፡፡ በፕሮግራሙ ከታቀፉ ወዲህ የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ከመሙላታቸው ባሻገር ሰርተው ከሚያገኙት መቆጠብ ጀመሩ፡፡ የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ብር ተበድረው ከቆጠቡትም በመጨመር የወተት ላም ገዝተው ማርባት ጀመሩ፡፡ አሁን ሁለት ምርጥ ዝሪያ የወተት ላሞች አላቸው፡፡ በቀን ከ1 ላም የሚገኘውን 12 ሊትር ወተት ለቤት ውስጥ ፍጆታም ተጠቅመው ሌላውን ለገበያ አቅርበው ገቢ ያገኛሉ፡፡ ጎን ለጎን ዶሮ ያረባሉ፤ ንብም ያነባሉ፡፡ በአመት ከ3 የንብ ቀፎዎች 15 ኪሎ ግራም ማር ያገኛሉ፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ፕሮግራሙ በነፃ ከሚያቀርባቸው የፍራፍሬና አትክልት ችግኞችም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ባላቸው ግማሽ ሄክታር እርሻ መሬታቸው ላይ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ሎሚ፣ ድሽጣ፣ ቡና፣ እንሰትና መኖ በማልማት በዓመት እስከ 50 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ወ/ሮ ብርቱካን ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ከፕሮግራሙ ያገኙትን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም የራሳቸውን ጥረት ጨምረው ኑሯቸውን መቀየር ችለዋል፡፡ ልጆቻቸውን በአግባቡ ያስተምራሉ፡፡ መኖሪያ ቤታቸውን ከሳር ወደ ቆረቆሮ ቤት ቀይረዋል፡፡ ልምዳቸውን ለሌሎችም እያካፈሉ ሲሆን ዘንድሮ ከፕሮግራሙ ለመመረቅ ዝግጁ ሆነዋል፡፡

አርሶአደር ኤሊያስ አብቾ ደግሞ  የዛቶሾደራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡  በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከታቀፉ ወዲህ 5 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከመታቀፋቸው በፊት አስከፊ ድህነት ውስጥ ነበሩ፡፡ እንደ አፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ የግብርና ግብዓቶችን ለመግዛት አቅም ስላልነበራቸው ያላቸውን አነስተኛ እርሻ መሬት በአግባቡ ማልማት አልቻሉም፡፡ እንኳን ልጆች ማስተማር ይቅርና ለመኖርም ከብዷቸው ነበር፡፡

በልማታውዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከታቀፉ ወዲህ ሰርተው ከሚያገኙት እየቆጠቡ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመግዛት አቅም ፈጥረው  ያላቸውን  እርሻ መሬታቸውን በአግባቡ ማልማት ጀመሩ፡፡ በተጨማሪ ፕሮግራሙ በነፃ የሚያቀርብላቸውን ችግኞች ተጠቅመው ፍራፍሬና አትክልት  ያለማሉ፡፡   እንሰት፣ ቡና፣  አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ድሽጣ፣ ፓፓያና የተለያዩ የመኖ ዓይነቶችን ያለማሉ፡፡ ጥሩ ገቢም ያገኛሉ፡፡ 1 ያረገዘች ምርጥ ዘር ግደርም ገዝተዋል፡፡ ዛሬ ኑሯቸውን አሻሽለው ልጆቻቸውንም በአግባቡ ያስተምራሉ፡፡

አርሶአደር ኤሊያስ ዘንድሮ ከፕሮግራሙ በራሳቸው ፈቃድ ለመመረቅ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ወደፊት ይበልጥ ተግተው በመስራት ከራሳቸውም አልፈው ሌሎች ችግራኞችን ለመርዳት ሀሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ፎቶግራፈር፡- ያሬድ አሰፋ

ዘጋቢ፡-    ሸምሱዲን ዩሱፍ