(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በኢትዮጵያ የእንስሳት ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ የእንስሳት በሽታን መከላከልና በዘላቂነት መቆጣጠር ላይ ሰፊ ተግባራቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የዓለም አቀፉ የእንስሳት ጤና ድርጅት (WOAH) የእንስሳት ህክምና አገልግሎት አፈጻጸም(PVS) የክትትልና ግምገማ ባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን የእንስሳት ህክምና አገልግሎት አፈጻጸም ለማየት ከግብርና ሚኒስቴር አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ እንዲሁም በእንስሳት ህክምና አገልግሎቱ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ላይ ለክትትልና ግምገማ ቡድኑ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) የእንስሳት ዘርፉ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የወጭ ንግድ ገቢ በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ወደ ምርታማነት ለመቀየር እየተሰሩ ካሉ ሰፋፊ ስራዎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ መሆኑን እና በዚህ ትግበራ የእንስሳት ጤና አገልግሎቱ ልዩ ትኩረት አግኝቶ እየተተገበረ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ዘመናዊ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት ከተመሰረተ በርካታ አመታት ማስቆጠሩንና በአሁኑ ሰዓት መዋቅሩ እስከ ቀበሌና አርሶአደሩ በመድረስ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ዶ/ር ፍቅሩ ገልፀው ይህንን የሚደግፉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች መኖራቸው ለእንስሳት ጤና ዘርፍ ትልቅ እድል መሆኑን አብራርተዋል፡፡


የእንስሳት ህክምና አገልግሎቱን ለማዘመን መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ሲሆን የእንስሳት ህክምና ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት የሰለጠኑ እና ልምድ ያላቸው የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎችን ማፍራት በመቻሉ ውጤታማ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ከአጠቃላይ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት አፈጻጸም ጋር የበጎችና ፍየሎች ደስታ መሰል በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ፕሮግራም ገፅታ ተጨማሪ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ በሚፈለገውና የአለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ደረጃ መሰረት ብቁ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ግዙፍና ደረጃቸውን የጠበቁ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዳሉ ገልፀው ማዕከላቱ በእንስሳት ጤና ምርምርና ምርመራ፣ በስልጠና እና ምክር አገልግሎት፣ ጥራት ያላቸው የእንስሳት ክትባቶች እና መድኃኒቶችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሀገራዊና ክፍለ-አህጉራዊ ደረጃ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራን እየደገፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ቀናቶች የክትትልና ግምገማ ቡድኑ በኢትዮጵያ በእንስሳት ጤና አገልግሎቱ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በመስክ በመገኘት ምልከታ የሚያደርግ ይሆናል፡
ዘጋቢ፦ ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፦ ዮዲት እንዳለው