/አዳማ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም የግብርና ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች ግብርናው በኢኮኖሚ ዘርፉ ያለውን የመሪነት ሚና የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማትና ክልሎች በዘርፉ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ስኬቶችና በታዩ ክፍተቶች ላይ ያተኮረ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ባለፉት አመታት በግብርናው ዘርፍ የነበሩ ማነቆዎች ተፈተው ወደ ስራ በመገባቱ በሁሉም የግብርና ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልፀው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰብልና ሆርቲካልቸር፣ በእንስሳት ልማት፣ በተፈጥሮሃብት ጥበቃ፣ በግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም በግብርና ወጭ ንግድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው አመት 30 ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት በማረስ 1.4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ 31 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን በ9 ወሩ 1.2 ቢሊዮን ኩንታል መሰብሰቡንና በመስኖ የተሸፈኑ መሬቶች ምርት ሲሰበሰብ የአመቱን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ስንዴን በመኸርና በመስኖ 7.7 ሚሊዮን ሄክታር ተሸፍኖ እየተሰራ ሲሆን ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በአመቱ መጨረሻ ይጠበቃል፡፡

በእንስሳት ዘርፉ ያለውን ሰፊ አቅም በመጠቀም ዘርፉን ቶሎ ኮሜርሻላይዝድ ለማድረግ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ እየተሰሩ ያሉት እና የመጡ ለውጦች ትልቅ እምርታ ማሳየታቸውን ዶ/ር ግርማ ተናግረው ባለፉት 9 ወራት 90 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ማሰራጨት መቻሉንና የቅድመ ወላጅ/ግራንድ ፓረንት ስቶክ/ የመጀመሪያውን የጫጩት ስርጭት ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዝርያ ማሻሻል፣ በዘመናዊ ቀፎ ስርጭትና አሳ ልማት ላይ የተሰሩ ስራዎች ለምግብ ዋስትናና ስነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ትልቅ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን በተፋሰስ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ለመገንባት የሚደረገው ጉዞ ምቹ መደላድል እየፈጠሩ መሆኑን ሚንስትሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አርሶአደሩና ማህበረሰቡ ላለፉት አመታት በነቂስ ወጥቶ የተራቆቱ መሬቶችን ለማልማት የተሰሩ ስራዎች ዘንድሮ እውቅና የሚሰጥበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የግብዓት አቅርቦት ለግብርናው ወሳኝ ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ግርማ በዘንድሮው አመት 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን ከ10.7 ሚሊዮን በላይ አገር ውስጥ መግባቱንና ስርጭት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የወጭ ንግዱን በማሳደግ ረገድ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ እና ተልዕኮውን እየፈፀመ ሲሆን ባለፉት 9 ወራት ከቡና ኤክስፖርት 1.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ሚንስትሩ ገልፀው በአመቱ የተያዘውን 2 ቢሊዮን ዶላር ለማሳካት በቀሪ ወራቶች በትጋት መስራት እንደሚገባ
አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ወደ ኤክስፖርት ንግዱ የማስገባት ስራ እተሰራ እንደሆነና ለዚህም ባለፉት 9 ወራት ስጋና የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ በመላክ 128 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን እና አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ሲታይ ግን አነስተኛ በመሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ዶ/ር ግርማ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በ9 ወራቱ ግብርናውን ዲጂታላይ ለማድረግ፣ አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት መሰራታቸውንና ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚያስችሉ አዋጆችና ደንቦች ወጥተዋል በቀጣይም እንደሚወጡ ዶ/ር ግርማ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ተከታታይ አመታት በዘርፉ የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም በተገኙ ውጤቶች ሳይዘናጉ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ትልቅ ኃላፊነት ከግምት በማስገባት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በውይይቱ ተነስቷል፡፡

ዘጋቢ ተዋበ ጫኔ
ካሜራ ያሬድ አሰፋ