/ይርጋ ጨፌ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ሂደት ውስጥ የተሳለጠ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርዓትን ማዘመንና መተግበር ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ አርሶአደሩን የመሬት ይዞታ ባለቤትነቱን በማረጋገጥ ምርታማና ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር የአርሶአደሩን የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በርካታ ሚሊዮን አርሶአደሮችም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ወስደዋል፡፡

ባለፉት አመታት ለአርሶአደሮች የተሰጡ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶች በአብዛኛው በሰብል አምራች አካባቢዎች ሲሆን በቡና አብቃይ አካባቢዎች ያሉ አርሶአደሮችን የይዞታው ማረጋገጫ ተጠቃሚ ለማድረግ ብሄራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርዓት(NRLAIS) በተንቀሳቃሽ መተግበሪያ በቡና የተሸፈኑ መሬቶችን የመቀየስና የመመዝገብ ፓይለት ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በቡና የተሸፈኑ መሬቶችን የመቀየስና የመመዝገብ ፓይለት ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮ ዞን ይርጋ ጨፌ ወረዳ ወግዳ ቀበሌ ላይ የፓይለት ፕሮጀክት ስኬታማ አፈጻጸም የይዞታ ሰርተፊኬት ስርጭት መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ ትዕግስቱ ገ/መስቀል ላለፉት በርካታ አመታት የአርሶአደሩን የመሬት ይዞታ የሚያረጋግጡ ሰርተፊኬቶች በመስጠት የአርሶአደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀው ይህም በአብዛኛው በሰብል አምራቾች አካባቢ እንደነበርና አሁን ደግሞ ቡና የሚያመርቱ አርሶአደሮች አካባቢ ላይ አዲስና አዋጭ ቴክኖሎጂ ፓይለት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሃገር በቡና የተሸፈኑ መሬቶችን የመቀየስና የመመዝገብ ፓይለት ፕሮጀክት በሶስት ክልሎች (ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች) እየተተገበረ መሆኑንና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስኬታማ አፈጻጸም ላይ በመድረስ ሰርተፊኬት መስጠቱ ሌሎች ተሞክሮውን እንዲያሰፉ የሚያስችል መሆኑን መሪ ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ቡና ወደ ውጭ ለመላክ የይዞታ ሰርተፊኬት አስፈላጊና አስገዳጅ እንዲሁም ለገዥዎች ዋስትና እየሆነ በመምጣቱ ቡናን በብዛት የሚያመርቱና ወደ ውጭ የሚልኩ አካባቢዎች ላይ የሰርተፊኬሽን አገልግሎቱን በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አቶ ትዕግስቱ አስገንዝበዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ኖህ ታደለ በበኩላቸው በክልሉ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውንና ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የአርሶአደሮችን የይዞታ መብት የማረጋገጥ ተግባር በማከናወን ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰርተፊኬት ማሰራጨት መቻሉን ገልፀው ቀሪ 1.5 ሚሊዮን ማሳዎች የልኬትና ምዝገባ ስራ የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የልኬትና ምዝገባ ስራ በሚጠይቁ ቦታዎች የቡና አብቃይ ወረዳዎች በስፋት የሚገኙ በመሆኑ በፓይለት ደረጃ የተጀመረው የቴክኖሎጂ አማራጭ ትልቅ እድል መሆኑን አቶ ኖህ ጠቅሰው ቴክኖሎጂው በየትኛውም መልክዓ ምድር፣ በየትኛውም የመሬት አጠቃቀም፣ ሽፋን፣ ልኬትና ምዝገባ ስራን ማከናወን የሚያስችል ጊዜና ሃብት ቆጣቢ እንዲሁም ጥራትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በይርጋ ጨፌ ወረዳ ወጊዳ ቀበሌ በግብርና ሚኒስቴር አጋርነት በስኬት የተፈጸመው የይዞታ ሰርተፊኬሽን ስራ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት በልዩ ትኩረትና ተነሳሽነት እንደሚሰራ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በፓይለት ፕሮጀክቱ የታቀፉ አርሶአደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ያሬድ አሰፋ