/አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
ሀገራዊ ለውጡ እውን ከሆነ በኋላ ባለፉት ተከታታይ አመታት የማክሮ ኢኮኖሚ እድገቱ አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን የግብርናው ዘርፍ ለእድገቱ የራሱን ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወር ሀገራዊና ተቋማዊ አፈጻጸም ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በአፈጻጸም ውይይቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት አይናለም ንጉሴ ግብርናው በተግባር ዘርፈ-ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልፀው ባለፉት 5 ዓመታት በምግብ እራስን ለመቻል የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት የመጣበት መሆኑንና ለዚህም ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት የተደረገው ጥረት በመስኖ ስንዴ ልማት መሳካቱንና አቅም መገንባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ገቡን ሚኒስትሯ ገልፀው፣ የእንስሳት ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የተመጣጠነ ምግብን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከግብርና ኢኒሼቲቮች በተጨማሪ በዘርፉ ባለፉት አመታት የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን ጨምሮ ሌሎች ሰፋፊ የግብርና እድገት ለውጦች መመዝገባቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብቻውን በቂ ስላልሆነ አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማረጋገጥ የተሻለ ስራ መስራትና ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ከተጀመረ ወዲህ ተግባራዊ እየተደረገና ውጤትም እያስመዘገበ ሲሆን ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አለም ወደ ሚመራበት የተሟላ ኢኮኖሚ እንደሚያደርሰው ክብርት አይናለም ጠቁመው በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራና በትብብር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ግብርናው የተግባር ቤት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ፣ ሪፎርሙ ቀጣይነት ባለው መንገድ ስኬታማ እንዲሆን የቴክኖሎጂ አቅርቦቶችንና አሰራሮችን በማሻሻል ግብርናውን ማሳደግ እንደሚገባና ለዚህም የግብርናው ቤተሰብ በተሻለና በላቀ አፈጻጸም ስራውን መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት በግብርናው ዘርፍ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ገበያ ተኮር የሰብል ምርትና ምርታማነት፣ ገበያ ተኮር የእንስሳትና አሳ ምርትና ምርታማነት፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም እና የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብርና ግብይት ማሳደግ ላይ የተሰሩ ስራዎች እቅዱን በማሳካት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡
የግብርና ቁጥጥር ስራዎች፣ ተቋማዊ የመፈፀም አቅምን ማሳደግ በተለይም የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቅ፣ የግብርና ዲጂታላይዜሽን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እና ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ የታየው አፈጻጸም ለቀጣይ የግብርናው ምርታማነት እድገት መደላድልን የፈጠሩ ናቸው፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ለአጠቃላይ የሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ድርሻው የጎላ ሲሆን አገሪቱ ከምትፈልገው እድገት ደረጃ አንጻር ግን ብዙ መስራት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ:- ተዋበ ጫኔ
ካሜራ:- ሬድ አሰፋ
ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦
ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et
ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia
ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia
ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews
ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia