FDRE Ministry of Agriculture

ግብርናው የአርሶ/አርብቶ አደሩን የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ፍላጐት የሚመጥን የኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት ይገባል፡- ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

/ኮምቦልቻ፣ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እና የተሻሻሉ አሰራሮችን በማስተዋወቅ በዘርፉ ለተሰማሩ ተጠቃሚዎች ምቹ እንዲሆኑ የግብርና ኮሌጆች ሚና የጎላ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ የአርሶ፣ አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮችን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲቻል የግብርና ሚኒስቴር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከደረጃ 4 በታች ያሉ ባለሙያዎችን የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ስልጠና በመጀመሪያ ዙር በኮምቦልቻና በአጋርፋ ግብርና ኮሌጆች 1,300 የቀበሌ ግብርና ልማት ባለሙያዎችን ወደ ኮሌጆች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም የፌዴራልና የክልል አመራሮች በተገኙበት የሙያ መሻሻያ ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በሁሉም የግብርና ዘርፎች የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ለውጥ መመዝገቡን እና በዘርፉ ለመጣው ለውጥ ከአርሶና አርብቶ አደሩ ግንባር ቀደም ሚና ጎን ለጎን የልማት ጣቢያ ሰራተኞች የማይተካ ሚና መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች ከ70 ሺ በላይ ግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞች በቀበሌ ደረጃ ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡  

እነዚህ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች የበርካታ አመታት የደረጃና አቅም ማሻሻያ ስልጠና እንዲሰጣቸው የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎችን ሲያነሱ መቆየታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ይህን ለመመለስ የግብርና ሚኒስቴርና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከግብርና ኮሌጆች ጋር በመሆን የሙያ ማሻሻያ ስልጠናው እንዲጀመር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ግብርናው ዛሬ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ እና ከአርሶ/አርብቶ አደሩ የእውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ፍላጐት ጋር ሲነፃፀር ውጤታማ እና ወጥነት ያለው የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት የእውቀትና የክህሎት ክፍተቶች እንዳሉ ሚኒስትሩ ጠቁመው  የችግሩ ዋና ምክንያት  በየቀበሌው ያሉ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ወቅቱ ከደረሰበት እድገት ጋር የሚመጥን ሥልጠና በአጭርና በረዥም ጊዜ እያገኙ ያለመሄድ መሆኑን በመገንዘብ ስልጠናው መጀመሩንና ይህ የግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞች ስልጠና በቀጣይ በሌሎችም የግብርና ኮሌጆች ተደራሽ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

በልማት ጣቢያ ሰራተኞች ከሚሰጠው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በተጨማሪ ባለሃብቱ በዘርፉ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ግርማ ጠቅሰው፣ የስልጠናው ውጤት የሚለካው የተገኘውን እውቀትና ክህሎት የአርሶና አርብቶአደሩን ምርታማነት ማሳደግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ላለፉት 7 አመታት ሀገሪቱ አዳዲስ የለውጥ መንገዶችን ይዛ ስትጓዝ በግብርናው የተጀመሩና የተሳኩ ኢኒሼቲቮች የኢትዮጵያን መልክ በአዎንታዊ የቀየሩ መሆናቸውንና  የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በዚህ ስራ ትልቅ አሻራ ማሳረፋቸውን ገልፀዋል፡፡

የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎች አገር ሰሪዎች መሆናቸውንና ባለፉት በርካታ አመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የደረጃ ማሻሻያ ፕሮግራም መፍትሄ ማግኘቱን ሚንስትሯ ገልፀው ሰልጣኞች በቂ እውቀትና ክህሎት በመላበስ አርሶና አርብቶአደሩን  በአዲስ ምክረሃሳብ፣ ቴክኖሎጂ፣ አሰራርና ትግበራዎች ልቀው መገኘት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ 

ሰልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታ በቂ ትጥቅና ስንቅ ይዘው በመውጣት የአርሶአደሩን የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመልሱ ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

ከስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ጎን ለጎን የግብርና ሚንስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የስራና ክህሎት ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በኮምቦልቻ ከተማ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በእንስሳት ማድለብና በወተት ልማት ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን እና የግል ዘርፍ አልሚዎችን እንዲሁም በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ የአፍሪካ ልህቀት ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ

ካሜራ፡-ማቲዎስ ተገኝ


ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦
ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et
ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia
ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia
ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews
ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia