/ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
ግብርና እንደ ሀገር መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ጉዞ የግብርናው ኢንቨስትመንት ጉልህ ሚና አለው፡፡
በሲዳማ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች አፈጻፀም፣ በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎና ሚና፣ በዘርፉ ያሉ መልካም እድሎች፣ በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያሉ ምቹ ሁኔታዎችና የታዩ ችግሮች ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሄዷል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ ግብርናው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህን ተልዕኮ ለማሳካት በአነስተኛ ይዞታ ከተሰማራው ብዙሃን አርሶ/አርብቶ አደሮች በተጨማሪ አገራችን ከዘርፉ የምትፈልገውን ውጤት ለማሳካት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ትልቅ ኃላፊነትና ድርሻ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንት ለወጭ ንግድ፣ ለእውቀት ሽግግር፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት አቅርቦት እና ለአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሰብሳቢው ገልፀዋል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንቱ በሚፈለገው ልክ እንዲያድግ መንግስት፣ ባለሀብቱና ባለድርሻ አካላት ተናበው ለአገራዊ እድገት መስራት እንዳለባቸው እና በዚህ ሂደት ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ሰለሞን አስገንዝበዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግብርናው ትራንስፎርም እያደረገ ሲሆን ይህንን ለማዘመን ዘርፉን በኢንቨስትመንት መደገፍ እንደሚገባና ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ባለሃብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን የሴቶች ተሳትፎ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የተሻለ ውጤት እያመጡ በመሆኑ ከዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማሳካት ሴቶችን ማበረታታትና ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያበረክት የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ የተሰማሩ ሌሎች ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ቦታዎችን በሚገባው ልክ በማልማት ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል፡፡
ግብርናው አዋጭ ቢዝነስ በመሆኑ በፋይናንስ መደገፍ ስለሚገባ ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ትክክለኛ የብድር ስርዓት ውስጥ ገብቶ መስራት እንዳለበት ተነስቷል፡፡
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ የግብርና ኢንቨስትመንት ሰፋፊ እርሻ ላይ በመሰማራት በአነስተኛ አርሶአደር ከሚመረተው ምርት በተጨማሪ በቂ ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ እንዲሁም በቂ የስራ እድል የሚፈጥር አመራጭ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ ክልል የግብርና ኢንቨስትመንት በግብርና ምርት ውል፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግና እሴት ሰንሰለት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ገልፀው ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ በሚደረገው ስራ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሲዳማ ክልል ያለውን የኢንቨስትመንት ነባራዊ ሁኔታ፣ ችግሮች፣ ማነቆዎችና መልካም አጋጣሚዎችን በማንሳት የመፍትሄ አቅጣጫዎች በመድረኩ ተቀምጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡-ያሬድ አሰፋ