FDRE Ministry of Agriculture

ምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል

(ሐዋሳ፣ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ በተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠርም የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ከክልሎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቴክኒካል ተልዕኮ ዙሪያ የውይይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ የውይይት መድረክ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራትን የሚሸፍን የሁሉም ክልሎች የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶች እንዲሁም በብሄራዊ ደረጃ የእያንዳንዱ ፕሮግራም ኮምፖነንት ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሔራዊ ማናጀር ከበሩ በላይነህ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የሁለተኛ ዓመቱን የትግበራ ወቅት እያጠናቀቀ በመሆኑ የትግበራውን ሂደትና የተገኘውን ተጨባጭ ውጤት በትክክል መለየት የሚያስችል ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንዲኖር ይህ የቴክኒካል ተልዕኮ በሲዳማ ክልል ፕሮግራሙ ተግባራዊ በተደረገባቸው ቀበሌዎች ላይ የመስክ ምልከታ እንደሚደረግ ገልፀው፣ ይህ ምልከታም የፕሮግራሙን ተፅዕኖ በቀጥታ በማህበረሰብ ደረጃ እንድንመለከት ያስችለናል ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ ክፍሌ ሻሾ በበኩላቸው፤ በክልሉ በ8 የገጠር ወረዳዎች እየተገበረ የሚገኘው ፕሮግራሙ በዚህም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አስተባባሪው አያይዘውም ፕሮግራሙ በዋናነት በክልሉ በሰብል ምርትና ምርታማነት ላይ፣ የአፈር ለምነት የማሻሻል ስራ፣ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳት መኖ ልማትና ጤና የመጠበቅ፣ የመስኖ ልማት ግንባታ፣ የገበያ መሰረተ-ልማት ስራ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የስርዓተ-ምግብና ስርዓተ-ጾታን የማጎልበት ስራ እንዲሁም የሴቶችንና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የዓለም ባንክ ተወካይ አያልሰው ይልማ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በፕሮግራሙ ባለፉት የትግበራ ወራት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ የፕሮግራሙ የትግበራ ወቅት ጥሩ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የሚያግዝ ውይይት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩም ፕሮግራሙ ተግባራዊ በተደረገባቸው ክልሎች ላይ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶች ማቅረብ የተጀመረ ሲሆን ውይይቱም ለሶስት ቀናት ይቀጥላል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶገራፈር፡- ዮዲት እንዳለው