የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ
በሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ሆኖ የሚከተለውን ተግባርና ኃላፊነት ይኖረዋል፡-
- የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍን ምርታማነትና ውጤታማነት ለማሻሻል ለአርሶ አደሩ፣ ለአርብቶ አደሩ፣ ለግል ባለሀብቱና በእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ለተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡ የኤክስቴንሽንና የስልጠና አገልግሎት እንዲስፋፋ ያደርጋል፤
- የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍን ምርታማነትና ውጤታማነት የሚያፋጥን የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና ፕሮግራም ሀሳቦችን በማመንጨት እንዲዘጋጁ ያደርጋል፣ ሲፈቀድም እንዲተገበሩ ያደርጋል፤
- ሀገራዊ ለአነስተኛ አርሶ እና አርብቶ አደር መስኖ ልማት የሚውል የውሃ ሀብት እንዲለይና ጥቅም ላይ እንዲውል ስርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል፣ አፈፃፀሙንም ይመራል፣ ይከታተላል፤
- ሀገራዊ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የተፋሰስና አግሮ ፎረስትሪ፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ የተሻሻሉ ዘመናዊ አሠራሮች ሥርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል፣ አፈፃፀሙንም ይመራል፣ ይከታተላል፤
- የተፈጥሮ ሀብት ልማት ምርምሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር የሚሰሩበት ስርዓት ይዘረጋል፣ ሲፀድቁም እንዲተገበሩ ያደርጋል፤
- የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ተመጋጋቢነት እንዲጎለብት ስርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል፣ ተግባራዊነቱን ይከታታላል፣ ይመራል፤
- የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍን ለማዘመን የሚረዱ ዕውቀትና ክህሎትን ለማሻሻል የሚያግዙ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ያደርጋል፤
- የደን ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም እንዲሁም ለደን ምርምር ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የሀገሪቱን ከፍተኛ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ የተቀናጀ የደን ልማት፣ የቁጥጥር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ያስተባብራል፤
- የአገሪቱን የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች በአግባቡ እንዲያዙ፣ እንዲጠበቁና የህብረተሰብ ጥቅም ተጋሪነት እንዲሰርጽ ይከታተላል፣የቅርብ አመራር ይሰጣል፤