FDRE Ministry of Agriculture

መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ግብርና ትንሳኤ ነው – አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ፣ (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርናው ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “በመደመር መንግስት እይታ የግብርና እመርታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው ስልጠናዎችን ለዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም የግብርና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት “የግብርና ልማት እሳቤዎች በመደመር ዕይታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ገለፃ እና ውይይት ተደርጓል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የመደመር መንግስት አቅጣጫ ያሉንን መልካም አጋጣሚዎችና ፀጋዎች በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን መቻል ነው።

የመደመር መንግስት የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚን በመከተል በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና ኢንደስትሪ ዘርፎች በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰው በዚህም ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የመደመር መንግስት የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የመደመር መንግስት እሳቤ የአቋም እና የእውቀት ድምር ነው ያሉት ሚኒስትሩ የሃገራችንን ግብርና ማሻገር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ለአብነትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እየተቋቋመ እንደሆነ ገልፀው ይህም ለማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ወጭ በእጅጉ የሚያስቀር ነው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ግብርና ትንሳኤ ማሳያ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

“የግብርና ልማት እሳቤዎች በመደመር ዕይታ” በሚል ርዕስ ለውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ(ዶ/ር) ናቸው፡፡

በመነሻ ፅሁፋቸውም፤ የምርምር የኤክስቴንሽን እና የአርሶ አደር ግንኙነት እንዲሁም አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለት ተዋናዮች ግንኙነት ምን እንደሚመስል አብራርተዋል፡፡

የግብርና ልማት እሳቤዎች በመደመር እይታ የተለያዩ እሳቤዎችን ተቀብሎ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ምን መስራት እንደሚገባም በፅሁፋቸው አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ተክለመድህን አቻምየለህ