የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አሁናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ በመሆኑ ግብርናውን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
(ወላይታ ሶዶ፣ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
የግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የተሻሻለውን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት እያስተዋወቀ ይገኛል።
ለፌደራልና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ለሚዲያ አካላት፣ ለግብርና ሚኒስቴር ቡድን መሪዎችና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ለግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ለ7 ክልሎች ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል።
በዛሬው ዕለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የፌደራልና የክልሉ አመራሮች በተገኙበት የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ትውውቅ ተደርጓል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መድረኩን ሲከፍቱ፤ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አሁናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ በመሆኑ ግብርናውን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
በኢኮኖሚ የገጠመንን ስብራት ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው ለዚህም የታሪክ እጥፋት ለማድረግ ግብርና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርና ቁልፍ ሴክተር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመው ለዚህም ያለንን የተፈጥሮ ጸጋና የሰው ሀብት ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግና እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ በማስቀጠል የምግብ ሉዓላዊነታችን ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤልያስ የቀድሞው ፖሊሲ ምርታማነትን በማሳደግ የነበረውን ሚና ገልጸው ክፍተቶቹን በመሙላት የተሻሻለ መሆኑን አስታውሰዋል።
ፖሊሲው የግል ዘርፎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መሆኑንና ግብርናን መሰረት ያደረገ መሰረተ-ልማት በመዘርጋት ከተማና ገጠሩን ለማስተሳሰርና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።
በሁሉም የግብርና ዘርፎች በተለይ (በአረንጓዴ አሻራ፣ በመስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት) አመርቂ ለውጥ መገኘቱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው ስኬቶችን ለማስቀጠል የፖሊሲው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) የፖሊሲውን ግብ ለማሳካት ዘርፉ በእውቀትና በብቃት መመራት አለበት ብለዋል።
ግብርና ለሁሉም ዘርፍ ምሰሶ ነው ያሉት ዶ/ር መሪሁን ሁሉም ዘርፎች ግብርናን መደገፍ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተስፋየ መንግስቴ (ዶ/ር) እና ሌሎች በተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የግንዛቤ ማስጨበጫ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶግራፈር፦ ዮዲት እንዳለው