FDRE Ministry of Agriculture

6ኛው ዓመታዊ የወጣቶች የአመራርና ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) 6ኛው ዓመታዊ የወጣቶች የአመራርና ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ “አረንጓዴ አሻራ ለዘለቄታዊ የግብርና ልማትና አረንጓዴ ኢኖቬሽን” በሚል መሪ ቃል መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዲሁም አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ከተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ በርካታ ወጣቶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት፣ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ተግተን በመነሳት፤ የሀገሪቱን የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ የማዘመን፣ የምግብ ዋስትናንና ብሔራዊ ክብርን የማረጋገጥ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን።

ዛሬ በወጣቶቻችን ላይ የምናደርገው እያንዳንዱ ኢንቨስትመንት፣ ለምንገነባት የበለጸገች ሀገር ሁነኛ ዓምድ ነው ያሉት አቶ ተመስገን ጥሩነህ አረንጓዴ ዐሻራን እያኖርን የትውልዱን የለመለመ ተስፋ እየተከልን፣ አረንጓዴና ዘላቂ የሀገር ግንባታን ለማፋጠን መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተጨማሪም ወጣቶች በግብርና፣ በሰላም ግንባታና በፖሊሲ ቀረጻ ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ ለማጠናከር መንግሥት አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ በ2019 (እ.ኤ.አ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከ17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደጉን ገልጸዋል።

ለዚህም ስኬት የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እ.ኤ.አ. በ2025 ለኢትዮጵያ የዘላቂ ደን አስተዳደርና አጠቃቀም ሽልማት ማበርከቱን አስታውሰዋል።

ወጣቶች በግብርና ትራንስፎርሜሽንና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ሚና እንዲጫወቱም ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው አሳታፊ ሲሆን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

በብሔራዊ የበጎ ፈቃደኝነት መርሃ-ግብር አማካኝነት ዜጎች በአረንጓዴ አሻራና በማህበረሰብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የኮንፈረንስ ማዕከል ለ3 ቀናት የሚቆየው ይህ 6ኛው ዓመታዊ የወጣቶች የአመራርና ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ፤ ወጣቶች በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዘላቂ ልማት እና በአረንጓዴ ኢኖቬሽን ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ለመጪው ትውልድ ዘላቂ አረንጓዴ አሻራ እንዲያስቀምጡ ለማበረታታት ታልሞ ተዘጋጅቷል።

በተጨማሪም መርሃ-ግብሩ ኢትዮጵያ ወደ COP32 በምታደርገው ዝግጅት ወጣቶች በቂ ዕውቀት፣ ክህሎት እና የዲፕሎማሲ አቅም እንዲገነቡ፣ የሀገራችንን የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎችና ቁርጠኝነት በአለም አቀፍ መድረኮች ለማስተዋወቅ የሚችሉ ወጣት መሪዎችን ለማብቃት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው

ፎቶ፦ ማቲዎስ ተገኝ