አዲስ አበባ፣ መስከረም 7/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) 2ኛው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል ከመስከረም 10 እሰከ 12/2019 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ይካሄዳል።
ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባለው የቴምር ዘርፍ ላይ ኢንቨስትመንትን፣ ፈጠራንና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር የቴምር አምራቾችን፣ ባለሀብቶችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የልማት አጋሮችንና ፖሊሲ አውጪዎችን በአንድ ላይ ያገናኛል።
ፌስቲቫሉ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በግብርና ሚኒስቴር እና Khalifa International Award for Date Palm and Agricultural Innovation በጋራ የተዘጋጀ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ፣ 2ኛውን የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ለቴምር ልማት ያላትን ከፍተኛ አቅም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከ500,000 እስከ 700,000 ሄክታር የሚደርስ ለቴምር ምርት ተስማሚ መሬት ያላት መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት እየለማ ያለው 1.2 በመቶ ብቻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የከርሰ ምድር ውሃና ሌሎች የውሃ አማራጮች ባሏቸው አካባቢዎች ልማቱን ማስፋፋት ሃገሪቱ ከውጭ የሚገባውን የቴምር ምርት ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በተለይም በቆላማ አካባቢዎች የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የKhalifa International Award for Date Palm and Agricultural Innovation ዋና ጸሐፊ ፕሮፌሰር አብደልወሃብ አልቡካሪ ዛይድ በበኩላቸው፣ ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል እያደገ የመጣው አጋርነት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለተኛው ኤክስፖ የመጀመሪያውን ስኬት መሠረት በማድረግ በእውቀት ሽግግር፣ በአቅም ግንባታ፣ በኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ፣ በተሻሻሉ የምርት ሂደቶች እና በምርምር ተቋማትና በገበያ መካከል ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሀሩን አሊ፣ የአፋር ክልል ለቴምር ምርት ያለውን ከፍተኛ አቅም ጠቁመው፣ ክልሉ ይህንን ዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ፌስቲቫሉ የክልሉን የግብርና አማራጮች ለማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና በአምራቾች፣ ተመራማሪዎችና የልማት አጋሮች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል ውጤታማ መድረክ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
