የሩዝ ሰብል ከብርዕና አገዳ ሰብሎች ውስጥ የሚመደብ ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የዓለም ህዝብ ዋና ምግብና የገቢ ምንጭ ነው፡፡
ሩዝ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1965 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ እና በሱማሌ ክልሎች እየለማ ይገኛል፡፡
የሩዝ ንጥረ-ነገሮች እንደ ዝርያው አይነት ቢለያይም በአብዛኛው ከ74 እስከ 79 በመቶ ካርቦሀይድሬት፣ ከ8 እስከ 9 በመቶ ፕሮቲን፣ ከ2 እስከ 2.4 በመቶ ቅባት የያዘ ሲሆን ሌሎች ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ የቫይታሚንና የፕሮቲን ንጥረ-ነገሮችን አሟልቶ የያዘ መሆኑን የተደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡
ሩዝ ከጠቀሜታው አንጻር ለተለያዩ ምግብና መጠጦች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እንዲሁም ገለባው ለእንስሳት መኖነት ሲያገለግል ጀንፈሉ ለማገዶነት ያገለግላል፡፡

🌾 ለሩዝ ልማት ተስማሚ ሰነ-ምህዳር
ከፍታ:- ሩዝ ከባህር ጠለል በላይ እሰከ 3000 ሜትር ሊለማ የሚችል ሰብል ነው፡፡ በተለይ ከ1500 ሜትር ከፍታ በታች ቦታዎች ላይ የበለጠ ይስማማዋል::
የአየር ሙቀት:- ከ18 እስከ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ ባለው የሚመረት ሲሆን ከ25 እስከ 35 ዲግሪ ሴልሺየስ የበለጠ ይስማማዋል፡፡
የዝናብ መጠን:- ሩዝን ለማምረት ከ800 ሚ.ሜ ያላነሰ ዓመታዊ ዝናብ ያስፈልገዋል፡፡ እስከ 2000 ሚ.ሜ ውሃ ቢያገኝ የበለጠ ይስማማዋል፡፡
ተስማሚ የአፈር ዓይነት:- ከቡናማ እስከ ኮትቻ/ጥቁር/ዋልካ አፈር ይስማማዋል፡፡
የአፈር ኮምጣጤነት፡- ለሰብሉ ተስማሚ የአፈር ጣዕም (Soil PH) ከ3.5 እስከ 8.5 ድረስ ነው፡፡
🌾 የሩዝ አዘራር ስልት/ዘዴ
የሩዝ ሰብል በቀጥታ ዘሩን ማሳ ላይ በመዝራት (Direct Seeding) እና ችግኝ አፍልቶ ወደ ዋናው ማሳ በማዛመት (Transplanting) ሊዘራ ይችላል፡፡
በቀጥታ ዘሩን ማሳ ላይ በብተና ወይም በመስመር ሊዘራ የሚችል ሲሆን ይህም የተሻለ ውጤት ያስገኛል፡፡
መንግስት በስንዴ ልማት የተገኘውን ስኬት በሩዝም ለመድገም በትኩረት እየሰራ ሲሆን ይህንንም ግብ ለማሳካት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
