FDRE Ministry of Agriculture

ፈተናን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ስኬታማ የሆነው ወጣት አርሶአደር


በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከምባታ ዞን፣ አዲሎ ዙሪያ ወረዳ፣ የሃሚዶ ቀበሌ ነዋሪ ነው ወጣት ሞዴል አርሶአደር አብነት ዴላሞ።
አርሶአደር አብነት የሚኖርበት አካባቢ በጣም በረሃማ እና የውሃ እጥረት የነበረበትና ለግብርና ስራ ምቹ ያልሆነ ነበር። ወጣቱ አርሶአደር ለዚህ ስኬት እንዲበቃ የለውጡ መንግስት ይዞት የመጣውን “በአካባቢያችን ያለውን ፀጋ በመለየት በአግባቡ መጠቀም” የሚለውን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረጉ ለስኬቱ መነሻ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በረሃማ የነበረው አካባቢ አረንጓዴ ለብሷል፡፡ ግቢው ባህላዊና ዘመናዊ ቤቶችን አካቶ በሀገር በቀልና የውጭ ዛፎች ተከቧል፤ በፋውንቴን የተዋበ፣ በጌጠኛ መተላለፊያ መንገዶችና በውብ አበቦች ያሸበረቀ እና በአእዋፍት ዜማ የታጀበው ግቢ መንፈስን በሃሴት ይሞላል፡፡ ወጣት አብነት በግቢው ዘመናዊ የሆቴል አገልግሎት (ሎጅ) የሚሰጥ መስሎ የሚታይ ለአይን ማራኪ የሆነ ልብን የሚያሞቅ፣ ምቹ እና ፅዱ የሆነ የምድር ገነት መፍጠር ችሏል።
በአንድ ወቅት በአካባቢው ያለውን የውሃ እጥረት በመቅረፍ የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎችን ለማከናወን ትልቅ የውሃ ገንዳ በማስቆፈር ከ5 ሺህ ሜትሪክ ኪውቢክ በላይ ውሃ መያዝ ችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን አጋጣሚ በተከሰተ ክስተት ይህ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ፈንድቶ ፈራረሰበት፤ የያዘውም ውሃ ጥቅም ላይ ሳይውል በአካባቢው ያለመማውን ነገር ሁሉ አበላሽቶበት መና እንዳስቀረው ያስታውሳል።

ነገር ግን ይሄ ፈተና ወድቆ እንዲቀር አላደረገውም፡፡ “በሚገጥሙን ፈተናዎች መሸነፍ ሳይሆን፤ ፈተናውን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ድል ማድረግ ይቻላል” የሚለውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሃሳብን ተግባራዊ በማድረግ የገጠመውን ፈተና ወደ ድል ቀይሯል።
ሞዴል አርሶአደር አብነት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከሶስት በላይ የተለያዩ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን በመቆፈር የግብርና ስራውን በትጋት ይሰራል፡፡ ግብርናን ለማዘመን የሚያስችል የምርምር ስራዎችን ለሚሰሩ ተመራማሪዎች ማረፊያ የሚሆን ሰፊ ሳሎን፣ ዘመናዊ የማብሰያ (ኪቺን) እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ የመኝታ ክፍል በመገንባትም ለተመራማሪዎች ተግባራዊ ጥናትና ምርምር እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽና ለተለያዩ እንግዶች ማረፊያ የሚሆን ዘመናዊ መኝታ ቤትን ገንብቷል።

ወጣት አርሶ አደር አብነት በ10 ሄክታር መሬት በሚሆን ግቢውና የእርሻ ማሳው ላይ የተቀናጀ ግብርናን ዕውን በማድረግ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሰብል ልማት፣ በቡና እና በቅመማቅመም ልማት እንዲሁም የገጠር ኮሪደር ልማትን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በዚህም ለ10 ወጣቶች በቋሚነት እና ከ50 እስከ 80 ለሚደርሱ ወጣቶች በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ብርቱ ወጣት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም በአካባቢው ለሚገኙ ከ4 መቶ በላይ የሆኑ አርሶአደሮችን በመደገፍ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እያገዘ ይገኛል፡፡
በቀጣይ አሁን ከሚያከናውነው የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ ባሻገር በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም እንደ ክልል እና እንደ ሃገር ትልቅ ፋይዳ ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችል ዘመናዊ የአርሶአደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት ትልቅ የተቀናጀ የግብርና ማዕከል ለመገንባት ከአካባቢው 50 ሄክታር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ይህንንም ህልሙን ዕውን ለማድረግ ምላሹን እየጠበቀ መሆኑን ነግሮናል።


በሃገር አቀፍ ደረጃ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወጣት አርሶአደር አብነት ዴላሞ የራሱን አሻራ ለማኖር ትልቅ ርዕይ ሰንቆ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በተጨማሪም በውሃ አጠር አካባቢዎች ላይ ውሃን በማሰባሰብ የግብርና ልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል በጥናት ላይ የተደገፈ ስራን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ወጣት አብነት ተናግሯል፡፡

እንደ ሞዴል አርሶአደር ወጣት አብነት አይነት የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ በርካታ አርሶአደሮችን በየአካባቢው መፍጠር ከተቻለ የብልፅግና ጉዞን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣት አርሶአደር አብነት የስራ ቦታ በመገኘት ምስክረነታቸውን እንደሰጡ የሚታወስ ነው፡፡


አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ

Agriculture #Ethiopia #AgriculturalTransformation
#ከማምረትበላይ #BeyondProduction

አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *