FDRE Ministry of Agriculture

ጥራት ያለው የስንዴ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22/2018 (ግብርና ሚኒስቴር)

የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት የዘር ቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች ለኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን እና ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ክልሎች ውስጥ ለአማራ፣ ኦሮሚያና አፋር ለ12 ቤተ-ሙከራዎች የሚሆኑ ቁሳቁሶች ርክክብ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ለቀሪ ክልሎች የሚሰጥ ይሆናል።

የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አብዱልሰመድ አብዶ ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ጋር የስንዴ ዘር ጥራትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት ርክክብ የተደረገባቸው የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች በክልሎች በስንዴ ጥራትና ፍተሻ ላይ ለሚሰሩት ስራዎች አጋዥ እንደሚሆኑ ጠቅሰው ርክክብ በተደረገባቸው እቃዎች ውስጥ አጉሊ ምንጽሮች (microscope)፣ ናሙና መውሰጃ መሳሪያዎች፣ መመዘኛና የእርጥበት መፈተሻ እንዲሁም ሎሎች መካተታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የመሳሪያዎቹ አጠቃላይ ወጪ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም በርክክብ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የዕፅዋት ዝርያና ዘር ሬጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሃ ተሾመ በበኩላቸው የአየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ከስንዴ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለመስራት በሚያስችል ሁኔታ ለባለስልጣኑ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት ለባለስልጣኑ እና ለክልሎች የተበረከቱት የቤተ ሙከራ መሳሪያዎች በዘር ጥራትና ፈተሻ ላይ ለሚሰራው ስራ ትልቅ አስተዋጾአ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡