FDRE Ministry of Agriculture

ጥራቱ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለጤናማ ትውልድ!

የምግብ ደህንነት ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን ሂደት ያካትታል፡፡ ምርት ሲመረት፣ ሲሰበሰብ፣ ሲጓጓዝ፣ ሲከማች፣ ምግብ ሲዘጋጅ ወይም ምገባ ላይ ለሰዎች ጤና ወይም ሕይወት አደገኛ የሆኑ ነገሮች የሌሉበት መሆኑን የማረጋገጥ ስራን ያጠቃልላል።

የምግብ ጥራት ምግብ የሚጠበቅበትን መደበኛ መስፈርት፣ ጣዕም፣ ውጫዊ መልክ እና የምግብ ይዘት አሟልቶ መገኘቱን ይመለከታል፡፡

የምግብ ደህንነትና ጥራት መጓደል መንስኤዎችና ጉዳቶቻቸው

የምግብ መበላሸትና ብክለት በተህዋሲያን፣ በፀረ-ተባይና ፀረ-አረም ኬሚካሎች እንዲሁም በእንስሳት መድሃኒት ቅሪት እና በባዕድ ነገሮች አማካኝነት ሊከሰት ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም የግልና የአካባቢ ንፅህናን ባለመጠበቅ፣ ጥሬና የበሰሉ ምግቦችን በአንድ ላይ መያዝ እና ተገቢ ባልሆነ የሙቀት መጠን ማከማቸት ለምግብ ደህንነትና ጥራት መጓደል ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ሲከሰቱ የምግብ መመረዝ፣ ስር የሰደዱ በሽታዎች እና የህፃናት መቀንጨር በመከሰት በጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዖኖ ከማሳደሩም ባሻገር የቤተሰብን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል፡፡

ለምግብ ደህንነት እና ጥራት መጓደል የመፍትሔ አካላት እና ሚናቸው

• መንግስት እና የቁጥጥር አካላት፦ ጥብቅ የህግ ማዕቀፎችን መተግበር፣ የግብዓት ጥራትና ደህንነትን ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

• የምርምር እና የትምህርት ተቋማት፦ ሕይወትን የሚታደግ ምርምር ማድርግ እና የምግብ ደህንነት ጥራት የሚያስጠብቁ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ማፈለቅና ለአርሶ/አርብቶ አደሩ እንዲደርስ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

• የልማት አጋር ድርጅቶች፡- መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት አጋር ድርጅቶች የምግብ ደህንነት እና ጥራትን የተመለከቱ ስራዎችን በመደገፍ ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ሚናቸው የላቀ ነው፡፡

• አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ዓሣ አጥማጆች እና የምግብ አምራቾች፡- የግብርና ምርትን በጥረት እና ደህንነቱ በጠበቀ መልኩ በማምረት መልካም የግብርና ምርት አሰራሮችን ሊተገብሩ ይገባል።

• የምግብ አቀናባሪዎች፣ ሰብሳቢዎች እና አጓጓዦች፡- የምግብ አቀናባሪዎች፣ ሰብሳቢዎች እና አጓጓዦች ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና አላቸው።

• ህብረተሰብ፦ ህብረተሰቡ የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ ምግብን በጥሩ ሁኔታ ማብሰል፣ ንጹህ ውሃ መጠቀም እና የምግብ ማሸጊያ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመልከት ይገባዋል።