FDRE Ministry of Agriculture

ግብርና እና ህክምና ተቀናጅተው ሲተገበሩ

ሀላባ፣ ነሐሴ 23/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀላባ ቁሊቶ ዞን አጠቃላይ ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ ውስጥ በ3 ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ ይገኛል፡፡

በሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ጎመን፣ ድንች፣ ቀይ ስር፣ ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ሮዝመሪ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ እንዲሁም ቡና እየለማ ሲሆን በዚህም ለ10 ሰዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

የእትክልትና ፍራፍሬ ምርቱ ለሆስፒታሉ ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ ሰራተኞች በነፃ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሌሎች ሰራተኞች ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው እየተጠቀሙ ነው፡፡

ከምርቱ ሽያጭ በሳምንት በአማካኝ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ ትርፉ ለህክምና ግብዓት ግዥ እየዋለም ይገኛል፡፡

የሆስፒታሉ ሜዲካል ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰለ ሙዳ ግብርና እና ጤና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ገልፀው ሁለቱንም ዘርፎች አቀናጅቶ መስራት ከተቻለ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ከልማቱ ትምህርት እንደተወሰደ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አትክልትና ፍራፍሬ እየለማበት ያለው መሬት ለበርካታ ዓመታት ጦም ያድር እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መሰለ ተቋማት ባላቸው ክፍት ቦታ የግብርና ልማት ስራን ቢሰሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በሆስፒታሉ ከአትክትና ፍራፍሬ ልማት ባሻገር የእንስሳት ልማትን በማካተት ልማቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ዕቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡