FDRE Ministry of Agriculture

ግብርናውን ለማዘመን ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ያለው ፕሮጀክት

ሻሸመኔ፣ ግንቦት 12/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የአካታች እና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት አርሶአደሩን ከባህላዊ የእርሻ አሠራር ወደ ዘመናዊ በማሸጋገር ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።


ፕሮጀክቱ አርሶአደሮችን፣ የግብርና ምርምር ማዕከላትን፣ የግብርና ምርት አቀነባባሪዎችን፣ ነጋዴዎችን፣ ወጣቶችን እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ተጠቃሚዎችን በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ በማቀናጀት እየሰራ ነው።

በተለይም የዳቦና ማካሮኒ ስንዴ፣ ቲማቲም፣ አቮካዶ እና አናናስ አምራቾችን ከቡልቡላና ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ ግብርናን ለማዘመን በኦሮሚያ ክልል እያንዳንዳቸው ማረሻና መከስከሻ ያላቸው 16 ትራክተሮች (14 ለዩኒየኖች፣ 2 ለግብርና ምርምር ማዕከላት)፣ 35 የመስኖ ውሃ ፓምፖችንና 3 የመኖ ቤለሮችን አስረክቧል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር አርሶአደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብርናውን ለማዘመንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ፕሮጀክቱ የማይተካ ሚና አለው ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ይህም የመስኖ ስንዴን ለማስፋፋትና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚ ማህበራትም እነዚህን የቴክኖሎጂ አቅሞች ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ ውጤት እንዲቀይሩ አሳስበዋል።

የአካታች እና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ዳኜ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ አርሶአደሮችንና ማህበራትን ከተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ ወጭን ለማዳን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ደመቀ አጥላው በበኩላቸው ድርጅቱ ለፕሮጀክቱ ስትራቴጂ፣ ቴክኖሎጂ እና የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ዲዛይንና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ድርጅቱ የገበያ ትሥሥር፣ መሰረተ ልማቶችና ቴክኖሎጂዎችን እያስፋፋ መሆኑን ተወካዩ ጠቅሰው፣ በፕሮጀክቱ ድጋፍ የተሰራጩት እነዚህ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ግብርናውን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶ፦ ዮዲት እንዳለው