FDRE Ministry of Agriculture

ዲጂታል ግብርና፤ መረጃ ወደ ምርት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢትዮጵያ ግብርና በተለምዷዊ አሠራር ብቻ ከመመራት በመረጃና ቴክኖሎጂ ወደተመሠረተ አሠራር እየተሸጋገረ ነው።

የአፈርና የአየር ንብረት መረጃን ከገበሬና ከገበያ መረጃ ጋር በማጣመር፣ ትክክለኛ የግብርና ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያስችል መረጃ ተኮር አሠራር እየተገነባ ነው።

የግብርና ሚኒስቴር በፈረንጆቹ ከ2025 እስከ 2032 የሚተገበረውን የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ በማስፈጸም ላይ ሲሆን ÷ ፍኖተ ካርታው 22 የዲጂታል አጠቃቀም ዘርፎችንና 32 የድጋፍ ተግባራትን ያካተተ ነው።

በዚህም የዲጂታል ግብርና አገልግሎቶች ከ10 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ገበሬዎች ተደራሽ ሆኗል።

ዲጂታላይዜሽን በተግባር የሚያመጣው ለውጥ በግብዓት አጠቃቀምና በምርታማነት ላይ የሚታይ ሲሆን ÷ በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተመሠረተ የማዳበሪያ ምክር ለገበሬው በመስጠት የግብዓት ብክነትን ማስቀረትና ምርትን ማሳደግ አስችሏል፡፡

‘ሃፋስ’ የተባለው የዲጂታል ማዳበሪያና አግሮኖሚ ምክር ሥርዓት በፈረንጆች 2025 ለ49 ሺህ ገበሬዎች ተደራሽ ሆኗል ፤ 2 ሺህ 700 የሚሆኑት ደግሞ ሥርዓቱ በመሬት ላይ የተረጋገጠባቸው ሙከራዎች ናቸው፡፡

የዲጂታል ምክር ሥርዓቱ መተግበሩን ተከትሎም በስንዴ ምርት ላይ ከ16 እስከ 25 በመቶ ጭማሪ ታይቷል፡፡

የአየር ንብረት መረጃን ለግብርና በተግባር ለማዋል የሚያስችል ብሔራዊ የዲጂታል አግሮ ክሊማት ምክር መድረክ የተዘጋጀ ሲሆን÷ መድረኩ የአየር ንብረት መረጃን በመተንተን ለገበሬዎች በተገቢው ጊዜና በአካባቢያቸው ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የግብርና ምክር ለመስጠት ያግዛል።

ይህም የመዝራት ጊዜን፣ የግብዓት አጠቃቀምንና የሰብል ጥበቃን በተሻለ ሁኔታ ለመወሰን በማስቻል የግብርናን ምርታማነትና የአየር ንብረት መቋቋም አቅም ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አለው።

በዚህም ገበሬው በግምት ከመወሰን ይልቅ በመረጃ ተመርኩዞ ሥራዎችን እንዲያፋጥን በማገዝ ውጤታማ እንዲሆን ያስችለዋል።

ከዚህ አኳያ ዲጂታል ግብርና መረጃን ወደ ውሳኔ፣ ውሳኔንም ወደ ምርትና ገቢ መቀየር የሚያስችል ውጤታማ እና ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዲጂታል ግብርና መርሃ ግብር “8028” ነጻ የስልክ መስመር በማዘጋጀት አርሶአደሮች መጠየቅ የሚፈልጉትን የግብርና መረጃዎች በሚፈልጉት ቋንቋ ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓል።

በተዘጋጀው ነጻ የስልክ መስመርም እስካሁን ድረስ ከ7 ሚሊየን አርሶአደሮች በላይ የተመዘገቡ ሲሆን ከ66 ሚሊየን በላይ ጥሪዎችን ተስተናግደዋል።

አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በሚገባው ዋጋ ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያግዝ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የምርቶችን ዋጋ ለማወቅ የሚያስችል “6777” ነጻ የስልክ መስመርም አለ።

እንዲሁም በአንድ አማካኝ ቦታ ላይ የተቀመጠ የግብርና መረጃዎችን የያዘ ዲጂታላይዝድ ኪዮስክ በማዘጋጀት አርሶአደሮች ወደ ኪዮስኩ በመሄድ ሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ግብርና የወደፊት ስኬት በመሬትና በሰው ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን በመረጃ ጥራት፣ በቴክኖሎጂ ተደራሽነትና በሚገኘው ምርት ይለካል።