FDRE Ministry of Agriculture

“የፀና ቃል፤ የላቀ እመርታ” በስንዴ ልማት የተገኘውን ስኬት በሩዝ ልማት መድገም!

ከብርዕና አገዳ ሰብሎች የሚመደብና ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የዓለም ህዝብ ዋና ምግብና የገቢ ምንጭ የሆነው ሩዝ በኢትዮጵያ በ1965 ዓ.ም አካባቢ መልማት ቢጀምርም ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሩዝን በስፋት ማልማት የሚያስችል ተስማሚ መሬት ያላት ሲሆን በዝናብ ወደ 6 ሚሊዮን ሄክታር እና በመስኖ 3.7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማት እንደሚችል የተደረገው ጥናት ያሳያል፡፡

መንግስት ሀገራችን ለሩዝ ልማት ያላትን ምቹ ስነ-ምህዳር ከግምት በማስገባት ባለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶት በመስራቱ አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡

በተለይም ግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የሩዝ ፍላግሽፕ ፕሮግራም ቀርጾ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የሩዝ ምርትና ምርታማነት እድገት እየፈጠነ ይገኛል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር ዋና ዋና ግቦች መካከል ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት አንዱ ሲሆን እንደ ስንዴ ሁሉ የሩዝ ምርትንም ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት እየተሰራ ነው፡፡

የሀገራችንን ከፍተኛ የሩዝ ፍጆታን ለመሸፈን ከውጪ የሚገባውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተደረገ ያለው ርብርብ በምርምርና ሜካናይዜሽን በመታገዙ ፈጣን ውጤት አስመዝግቧል፡፡

በየዓመቱ እያደገ የመጣው የሩዝ ምርትና ምርታማነትም የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በ2012/13 ምርት ዘመን 2.76 ሚሊዮን ኩንታል የነበረውን የሩዝ ምርት በ2016/17 ምርት ዘመን 64.4 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡

በአማራ ክልል የተጀመረው የሩዝ ልማት ዛሬ ላይ ከሲዳማና ሀረሪ ክልሎች በስተቀር ወደ ሁሉም ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን የሩዝ ልማት ስራን ከማስፋፋት ባሻገር ከኩታ-ገጠም እርሻ አሰራር በተጨማሪ ልማቱን በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በስንዴው ልማት የተገኘው ስኬት በሩዝ ልማትም ይደገማል፡፡

አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ

ፎቶ፡- ዮዲት እንዳለው