FDRE Ministry of Agriculture

የግጦሽ መሬት ላይ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት የሚያስችል ስርዓት

ሰመራ፣ ግንቦት 1 ቀን 2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ክትትል ስርዓት ላይ ውይይት እና ስርዓቱን በአፋር እና በድሬዳዋ አስተዳደር በይፋ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የፌደራልና የክልል ተወካዮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በአፋር ክልል ምክትል ፕሬዘዳንትና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዑመር ኑር የግጦሽ መሬት ሁኔታን በወቅቱ ለመከታተልና በትክክል መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ክትትል ስርዓትም የግጦሽ መሬት ላይ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ፕሬዘዳንቱ አክለውም የመረጃ ስርዓቱ በአፋር ክልል የግጦሽ መሬት ሃብትን ለመጠበቅና የልማት አቅጣጫዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ አንስተው ስርዓቱን ያዘጋጁትን ግብርና ሚኒስቴርን፣ የአትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንዲሁም ለሌሎች አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ በበኩላቸው የክልሉ ህዝብ ኑሮ በዋናነት የተመሰረተው በእንስሳት ሃብት እና በግጦሽ መሬት ሃብቶች ላይ መሆኑን ገልፀው ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ክትትል ስርዓት የግጦሽ መሬት ሃብቶችን በትክክል ለመረዳት፣ ለመጠበቅ እና በዘላቂነት ለማስተዳደር ሚናው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የእንስሳት ሃብት ኮሜርሻላይዜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ዮሴፍ መካሻ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት 60 በመቶ መሬት የአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች መሆኑን በመግለፅ በዚህም 15 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መተዳደሪያ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የግጦሽ መሬቶች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ክትትል ስርዓቱ በዲጅታል ሳተላይት ቴክኖሎጂ በመታገዝ የግጦሽ መሬት ሁኔታን ለመከታተል እና ለፖሊሲና ለልማት ውሳኔዎች የሚያገለግል ወቅታዊ መረጃ ለማቅረብም ሚናው የላ ነው ብለዋል፡፡

ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ክትትል ስርዓቱ በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ በመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም በአለም ባንክ ትብብር ተዘጋጅቷል፡፡

የመረጃ ስርዓቱ በአፋር፣ ሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚተገበር ሲሆን በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ይፋ ተደርጓል፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ