ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 28/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች፣ የክልል ግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች አዲሱን የቢሾፍቱ አለምአቀፍ የመንገደኞች አውሮፕላን ማረፊያን ጎበኙ፡፡
አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች አውሮፕላን ማረፊያ፣ ከአዲስ አበባ 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ፣ ከባሕር ጠለል በላይ በ1,910 ሜትር ከፍታ ላይ እየተገነባ ይገኛል።
ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ አሁን ካለው የቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የማስተናገድ አቅም ጋር ሲነጻጸር በ4.4 እጥፍ ብልጫ ይኖረዋል።

ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት፣ ሀገራችንን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ በደረሰበት ሁሉ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርጎ የሚያሳይና የአህጉራችን ኩራት በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት በአፍሪካና ከዚያም ባሻገር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ሌሊትና ቀን በከፍተኛ ጥረት እየተገነባ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች፣ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የላቀ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ሞዴል ዴስክ ሃላፊዎችና ቡድን መሪዎች እንዲሁም ባለሙያዎች በቢሾፍቱ እየተገነባ የሚገኘውን የቢሾፍቱ አለምአቀፍ የመንገደኞች አውሮፕላን ማረፊያን እንዲሁም በግንባታው ከቦታቸው ለተነሱ አርሶአደሮችና የማህበረሰብ ክፍሎች የተገነቡ የመኖሪያ ቤት፣ የንግድ ማዕከላት፣ የትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
