FDRE Ministry of Agriculture

የግብርና ኢንቨስትመንት እመርታ!

የግብርና ኢንቨስትመንት በአስር ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ ውስጥ በትኩረት እንዲሰራባቸው ከተለዩ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን በማህበረሰብ ውስጥ የማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ እና ሰፊ የስራ ዕድልን የመፍጠር ግቦችን ለማሳካት የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም በመጠቀም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እየሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በእርሻ ኢንቨስትመንት ብቻ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በ 8 ሺህ 904 ባለሀብቶች እጅ ይገኛል።

መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ በመሬት አቅርቦት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በማመቻቸት፣ በውል እርሻ (Contract Farming) በተሰማሩ አስመራቶች በኩል አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ እና መሰረተ-ልማትን ከማመቻቸት አንጻር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ሽግግር የሚያፋጥኑ ሀገር በቀል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለግብርና ባለሀብቶች የማስተዋወቅ ስራም በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርና ኢንቨስትመንት ዙሪያ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል። ለአብነትም የዘርፉን አሰራር ለማዘመን የኮንትራት እርሻ፣ የምርጥ ዘር ብዜት እንዲሁም አካታች የኤክስቴሽን የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡

አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ሰብል እና እንስሳት በኢንቨስትመንት ደረጃ እየለሙ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለወጪ ንግድ እየቀረቡ ሲሆን በሁሉም ምርቶች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ከወጪ ንግድ የተገኘ ገቢ አፈፃፀም ስንመለከት በ2013 ዓ.ም 309,866.8 ቶን ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 531,480 ዶላር የተገኘ ሲሆን በዘንድሮ 10 ወራት ደግሞ ከ236,415.3 ቶን ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 408.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡

የእንስሳት ኢንቨስትመንት ለሀገራዊ ኢኮኖሚ፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር፣ ለምግብ ዋስትናና ለገጠር ኑሮ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በእንስሳት ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች የተላለፈው አጠቃላይ መሬት 112 ሺህ ሄክታር መሬት ሲሆን በእርሻና ሆርቲከልቸር ኢንቨስትምንት ደግሞ 643 ሺህ ሄ/ር መሬት መተላለፍ ችሏል፡፡

አዘጋጅ፡- ዮሐንስ ደመቀ