(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
የግብርና ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድልን በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ለማክሮ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በግብርና ኢንቨስትመንት 2.5 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት እያለማ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ እንደገለጹት የግብርና ኢንቨስትመንት ለትልልቅ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው።

የግብርና ምርት ግብይትና ኤክስፖርትን ለማሻሻል ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህም በክልሎች የሰብል አምራችና ላኪ ማህበራት መቋቋሙን እና የግብርና ምርት ውል የአምራች አስመራች ግንኙነት ለመወሰን የወጣው አዋጅም ለግብርና ኢንቨስትመንት ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ኢንቨስትመንት ችግሮችን ለመቅረፍ በፌደራልና በክልል ደረጃ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም መካሄዱን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።
ይህም የግብርና ባለሀብቶች የሚያቀርቧቸውን የመሰረተ ልማት (መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ኔትወርክ) ጥያቄዎች ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
የከምባታ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ትርንጎ ጴጥሮስ የግብርና ኢንቨስትመንት በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በደን ልማት ለውጦች እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
ከምባታ ዞን ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ ባለሀብቶች በውስን መሬት በከብትና ንብ እርባታ፣ በማድለብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ብዙ ማምረት እንደሚቻል አሳይተዋል ብለዋል።
ባለሀብቶች በሜካናዜሽንና በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችና መኖ በማቅረብ ረገድ ለአርሶአደሮች በማሳየት ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ኃላፊዋል ተናግረዋል።
ከወተት ልማት ባሻገር የተቦረበረ መሬትን በማልማት የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን 950 ሺ ዛፍ (ግራቪሊያ) ያለማውን የከነዓን የጥምር ግብርና ኢንቨስትመንት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የከነዓን የጥምር ግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተክሌ ኃ/ማርያም በ20 ሄ/ር መሬት ላይ በወተት ልማት፣ በደንና በሌሎች ልማቶች ለ200 ሰራተኞች የሥራ እድል ጠቅሰው ኢንቨስትመንቱ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም በማድረግና ደን በማልማት የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ሰራሽ መንገድ በማዳቀል፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና የወተት ተዋጽኦዎችን ተደራሽ በማድረግ ኢንቨስትመንቱ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለውም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አመተረፍ ሁሴን በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች በውስንና በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አኳያ ት/ቤቶችንና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን በመገንባት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉራጌ ዞን በአበባ ልማት ከተሰማሩ ኢንቨስትመንቶች አንዱ የቲናው ቢዝነስ አ.ማ ሲሆን በ7 ሄ/ር የጀመረው የአበባ ልማት አሁን 100 ሄ/ር መድረሱንና ለ1600 ሰራተኞች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የቲናው ቢዝነስ አ.ማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መስፍን ኃይሌ ከ20 በላይ የአበባ ዓይነቶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ በመላክ የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ ለሀገራዊ ዕድገት አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ለአካባቢው በውሃ አቅርቦት፣ መንደሮችን የሚያገናኝ መንገድና ድልድይ በመሥራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ያሉት አቶ መስፍን፣ በአበባ ልማቱ አካባቢ በሳምንት የማያቋርጥ ገበያ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ ከቲናው ቢዝነስ አ.ማ የጊዜ አጠቃቀምና የሥራ ባህል፣ የኮምፖስት አዘገጃጀትና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ትምህርት እየቀሰመ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶግራፈር፦ ያሬድ አሰፋ