ጅማ፣ ሚያዝያ 9/2018 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) በኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ለማጠናከር ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ የዘርፉን መረጃ ልውውጥ ስርዓት ዲጂታላይዝ ማድረግ ነው፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንት መረጃዎች አካታች፣ እርስ በእርሱ ተናባቢና የላቀ ፈጠራን ተንተርሰው ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የተናበበና የተሳለጠ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና 2030 መርህ መሰረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ከጀርመን የልማት ትብብር (GIZ) ጋር በመተባበር ከኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር እና ጅማ ዞኖች ለተውጣጡ ግብርና ኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በግብርና ኢንቨስትመንት መረጃዎች ዲጂታል ስርዓት አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም በመጠቀም በርካታ ባለሃብቶች በዘርፉ መሰማራታቸውን ጠቅሰው፣ ዘርፉን ለማስፋፋት መንግስት በመሬት አቅርቦት፣ በፋይናንስ አገልግሎት እና መሰረተ ልማት ከማመቻቸት አኳያ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከመሬት ልማት ጀምሮ አጠቃላይ የግብርና ኢንቨስትመንቱን እንቅስቃሴ በተጨባጭ መረጃ ታግዞ መደገፍና የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ በተዋረድ እንዲኖር የግብርና ኢንቨስትመንት መረጃዎች በዲጂታል ስርዓት እንዲሳለጡ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡

ለዚህም የግብርና ኢንቨስትመንቱን የሚደግፉ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የዘርፉን መረጃዎች በዲጂታል ስርዓት መስራት የሚያስችል ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰጡ እንደሆነም ተገልጾአል፡፡

ለግብርናው ምርታማነት እድገት ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን በወቅቱና ለታለመለት ቦታ ተደራሽ ለማድረግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማፋጠን እና ለአፈጻጸምና ውሳኔ አሰጣጥ ምቹ ለማድረግ የመረጃ ስርዓቱን ማዘመንና ዲጂታላይዝድ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም ኢንቨስትመንቱን በአግባቡ ከታች ወርዶ ለመደገፍና እርስ በእርሱ የተናበበ መረጃ እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ማቲዎስ ተገኝ
#ከማምረትበላይ #BeyondProduction
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት👇
📌ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et
📌ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia
📌ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia
📌ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews
📌ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia
📌ሊንክድኢን፡- https://shorturl.at/7O6cs
📌ቲክቶክ፦ http://www.tiktok.com/@moaethiopia
📌ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/moa_ethiopia/
