FDRE Ministry of Agriculture

የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የምርምር እና የባለሃብቱን ትብብር ማጠናከር

ጅማ፣ ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የመልማት ፀጋ ወደ ምርታማነት በመቀየር ረገድ የዘርፉ ባለሃብቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡

የዘርፉ ባለሃብቶች ያሉባቸውን የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን በመሙላት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ከግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር የትብብር ስራን እንዲያጠናክሩ ማድረግ ይገባል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ከጀርመን የልማት ትብብር(GIZ) ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ከቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር እና ከጅማ ዞኖች የግብርና ኢንቨስተሮች ጋር  ባሉ ምቹ ሁኔታዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር በሚደረጉ የቴክኖሎጂ ትብብር ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ወደ ልማቱ ሲሰማሩ በምርምር የተለቀቁ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 

ለዘርፉ ኢንቨስትመንት እድገት ከፖሊሲና ህግ ማዕቀፎች ጀምሮ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የዘርፉ ኢንቨስተሮች እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀምና በዘርፉ የሚያጋጥሟቸውን የምርምር ቴክኖሎጂ እጥረት ለመፍታት ከምርምር ማዕከላት ጋር   ትብብርን ለማጠናከር በጋራ እየሰሩ ነው፡፡

የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ለኢንቨስትመንቱ የሚሆኑ በርካታ የቡና፣ የአኩሪ አተር፣  የሆርቲካልቸር፣ የእንስሳት እና ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን የለቀቀ ሲሆን በቀጣይ ከባለሃብቶች ጋር በቅንጅት በመስራት የተሻሻሉ ዝርያዎችን እና የምርምር ውጤቶችን ተደራሽ እንደሚያደርግ በምክክር መድረኩ አንስቷል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን ኖፓ ወረዳ የሚገኘው የዘማቹ ገመዳ የቡና እርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ ሌንሴ ያደታ እርሻ ልማቱ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማስመዝገብና ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከላት የሚለቋቸውን የተሻሻሉ ዝርያዎችንና የምርምር ቴክኖሎጂዎችንም በአግባቡ  እየተጠቀሙ መሆኑን ስራ አስኪያጇ ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ

ፎቶግራፈር፡- ማቲዎስ ተገኝ

#ከማምረትበላይ #BeyondProduction