አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላት ይፋዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ እንደተናገሩት የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ የግብርናውን ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡
የኩታ-ገጠም እርሻን አሁን ላይ 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መድረሱን ተናግረው በዚህም የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በማሳደግ አርሶና አርበቶ አደሩን ወደ ኢንቨስትመንት ኩባንያ እንዲሸጋገሩ ያስችላል ብለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶና አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮችን በኩባንያ በማደራጀት ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በኩባንያ በማደራጀት መሬት የመጠቀም መብታቸውን፣ የእንስሳት ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን ወደ ካፒታል በመለወጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ግልጽ የህግ ማዕቀፍ ለመደንገግ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የፖሊስ ጥናት፣ ስትራቴጂና ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ተስፋየ መንግስቴ (ዶ/ር) የግብርና ቢዝነስ ኩናንያን ረቂቅ አዋጅን ለባለድርሻ አካላት ገለጻ አድርገዋል።

በመድረኩ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት አመራሮችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ተዋንያን እየተሳተፉ ተሳትፈዋል።

ምክር ቤቱ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅን፤ አዋጅ ቁጥር 20/2018 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ የሚታወስ ነው፡፡
