የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባ ላይ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ ቁጥር 1433/2018 ሆኖ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ መፅደቁ ይታወሳል፡፡
የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በሀገራችን የግብርና ዘርፍ በአነስተኛ አምራች አርሶና አርብቶ አደሮች መካከል ለዓመታት የነበረውን መዋቅራዊ ክፍተት የሚሞላና አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
ይህ አዋጅ ቀደም ሲል አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች መሬት የመጠቀም መብት እንዲሁም የእንስሳት ሃብትና ጉልበት ቢኖራቸውም፤ ሃብታቸውን እንደ ድርሻ በማዋጣት ወደ ካፒታል የሚቀይሩበትና በኩባንያ ደረጃ የሚንቀሳቀሱበት ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም።
አዲሱ አዋጅ ይህንን ክፍተት በመሙላት፣ አነስተኛ አምራቾች በክላስተር ተደራጅተው የራሳቸው የሕግ ሰውነትና ጠንካራ የኮርፖሬት መዋቅር እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር ይህ አደረጃጀት አምራቾች ያላቸውን ሃብትና ጉልበት ወደ ካፒታል እንዲለውጡ፣ የፋይናንስና የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙና ምርታቸውን በከፍተኛ መጠንና ጥራት ሰብስበው እሴት በመጨመር በገበያ ላይ ጠንካራ የመደራደር አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል።
የአዋጁ ዋና ዋና ጥቅሞች፡-
➜ መሬት የመጠቀም መብትንና ጉልበትን ወደ ካፒታል መለወጥ
➜ አምራቹ አርሶና አርብቶ አደሮች ጠቃሚ ሀብት እያለው በካፒታል እጥረት ምክንያት ኋላቀር በሆነ አሠራር ውስጥ እንዲቆይና ከዘመናዊ የቢዝነስ ዓለም እንዲገለል አድርጎታል።
➜ አምራቾች መሬት የመጠቀም መብታቸውን፣ የእንስሳት ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን በመጠቀምና ካምፓኒ በማቋቋም ንግድ ማካሄድ እንዲችሉ አዲሱ አዋጅ ይፈቅዳል።
የግብርና ቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት መሻሻል
➜ አምራቾች በኩባንያ ሲደራጁ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦቶችን ማለትም የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽኖችና
የአመራረት እውቀቶችን በጋራና በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ ቀላል ይሆናል። ይህም ምርትና ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
➜ የገበያ መደራደር አቅምን ማሳደግና ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት
አነስተኛ አምራቾች በተናጠል በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በገበያ ላይ የመደራደር አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ አያገኙም ነበር። አዋጁ አምራቾችን በኩባንያ በማደራጀት ምርትን በከፍተኛ መጠንና ጥራት የመሰብሰብና የማከማቸት አቅም ይፈጥራል።
እሴት በመጨመርና የንግድ አሠራርን በማዘመን፣ አርሶና አርብቶ አደሩ በአምራችነት ብቻ ሳይወሰን በገበያ ላይ ጠንካራ የመደራደር አቅም ፈጥረው ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላቸዋል።
የፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ
ቀደም ሲል የተበታተኑ አነስተኛ አምራቾች የፋይናንስ አገልግሎቶችን (የባንክ ብድር ወይም የኢንሹራንስ ዋስትና) ለማግኘት በግል ደረጃ የሚጠየቀውን ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ የብድር ዋስትና (Collateral) ማቅረብ ባለመቻላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ትልቅ ተግዳሮት ሆኖባቸው ቆይቷል።
በአዲሱ አዋጅ መሠረት አምራቾች በጋራ በኩባንያ መዋቅር ሥር መደራጀታቸው ለፋይናንስ ተቋማት አስተማማኝ የጋራ የብድር ዋስትና (Corporate Collateral) ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት ለአምራቾቹ በቀላሉና በሰፊው ብድርና የመድን ዋስትና እንዲያቀርቡላቸው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የገጠርና ከተማ እንዲሁም የግብርናና ኢንዱስትሪ ትስስር
አዋጁ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕውን መሆን ትልቅ መዋቅራዊ ድልድይ ይሆናል፡፡ በገጠር የሚመረተው ምርት በቀጥታ ለከተማው ገበያና ለሀገር ውስጥ አግሮ-ኢንዱስትሪዎች (ለምሳሌ ለምግብና መጠጥ ፋብሪካዎች) በጥራትና ያለማቋረጥ እንዲቀርብ በማድረግ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ያስተካክላል።
በተጨማሪም አምራቾች በምርታቸው ላይ እሴት በመጨመር ምርቱን በቀጥታ ለዋናው ገበያ በማቅረብ የገቢ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ሲሆን ይህ የተቀናጀ የገበያና የኢንዱስትሪ ትስስር የገጠር አምራቾች የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢና የንግዱ ማህበረሰብ ቀጥተኛ ባለድርሻ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ሰፊ የሥራ ዕድልና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ይፈጥራል።
በአጠቃላይ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ የተበታተኑ አነስተኛ አምራቾችን ወደ መካከለኛ አምራችነት በማሸጋገር፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመንና ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ሽግግር ዕውን መሆን መሠረት የሚጥል ትልቅ የፖሊሲ ስልት ነው።
