/አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የግብርና ምርት ውል (የኮንትራት እርሻ) በተጨባጭ ውጤት እያመጣ ሲሆን የግብርና ምርትን በመጠን፣ በጥራትና በአመራረት ቅልጥፍና ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር የግብርና እና የአግሮ-ኢንዱስትሪ ተመጋጋቢነትን እያሳደገ ይገኛል፡፡
የኮንትራት እርሻ አስመራቾች እና አምራቾችን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን ከተጠቃሚ አስመራቾች መካከል ሳማኑ ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ሳማኑ ድርጅት በኦሮሚያ ክልል ከዱከም ከተማ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ አለው፡፡

ድርጅቱ በግብርና ምርት ውል ስምምነት መሰረት በጅማ ዞን በተመረጡ 7 ወረዳዎች ውስጥ ወደ ኢንቨስተርነት ተሸጋግረው ሰፋፊ እርሻ ከሚያለሙ አርሶአደሮች እና ከአነስተኛ እርሻ ባለይዞታ አርሶአደሮች ጋር እየሰራ ነው የሚገኘው፡፡
ሳማኑ ድርጅት ውል ገብቶ ከመስራቱ በፊት በቀርሳ ወረዳ ውስጥ የእርሻ መሬትን ኮንትራት በመውሰድ በ18 የሱፍ ዓይነቶች ላይ የሙከራ ስራ ሰርቷል፡፡ በዚህም ከአካባቢው ጋር የሚስማማና ከፍተኛ ምርት የሚሰጠው የትኛው የዝሪያ ዓይነት እንደሆነ ከለየ በኋላ ነው ወደ ስራ የገባው፡፡
በዚህ መሰረት በ2017/18 ምርት ዘመን በአኩሪ አተር ልማት ላይ ከተሰማሩ ከ23 ሰፋፊ እርሻ አምራች አርሶ አደሮች ጋር በ1300 ሄክታር መሬት ላይ ወል አድርጎ እየሰራ ሲሆን ከ1044 ባለአነስተኛ እርሻ ይዞታ አርሶአደሮች ጋር በ370 ሄክታር መሬት ላይ በሱፍ ምርት ላይ ተዋውለው እየሰራ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ድርጅቱ በግብርና ምርት ውል ስምምነት መሰረት በ1670 ሄክታር መሬት ላይ በአኩሪ አተርና በሱፍ ልማት እየሰራ ሲሆን በአኩሪ አተር ከ1 ሄክታር በአማካይ 25 ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡

ድርጅቱ በፊት እነዚህን ምርቶች (ግብዓት) ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ዜይትን ሲያመርት ነበር፡፡ አሁን ግን በግብርና ምርት ውል መሰረት እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት እየሰራ ነው ያለው ፡፡
በዚህም ከግብርና ምሰሶች ውስጥ እንዱ የሆነውን ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ሂደትን እያፋጠነ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ ከዘር አቅርቦት ጀምሮ ሰብሉ እስኪሰበሰብ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እየሰጠ በጥራት የተመረተውን ምርት በቅርበት በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ ከማግኘቱ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡

አቶ አህመድ አብዱልአዚዝ ወደ ኢንቬስተርነት ተሸጋግረው በኮንትራት እርሻ ውል መሰረት ከሳማኑ ድርጅት ጋር ተዋውለው ሰፊ እርሻ ከሚያለሙ አምራቾች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ዘንድሮ በሰኮሩ ወረዳ በቤዴ ቀበሌ ውስጥ መንግስት ከሰጣቸው 100 ሄክታር መሬት ውስጥ 45 ሄክታር በአኩሪ አተር አልምተዋል፡፡ ለአቶ አህመድ በሁሉም ነገር ከድሮ ዘንድሮ እጅግ የተሻለ ነው፡፡
አርሶአደር ሐጅ አባረሻድ ሼክአደም ደግሞ በስምምነቱ መሰረት ከድርጅቱ ጋር ከሚሰሩ ከአነስተኛ እርሻ ባለይዞታ አርሶአደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኦሞ ናዳ ወረዳ የጮሌ ቤየም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ዘንድሮ በ6 ጥማድ እርሻ መሬታቸው ላይ አኩሪ አተር አልምተዋል፡፡
አርሶአደር ሐጅ አባረሻድ በአኩሪ አተር ልማት ዘንድሮ የመጀመሪያቸው ቢሆንም ሰብሉ ጥሩ ስለያዘ ጥሩ ምርት ሲጠብቁ ወደፊት ደግሞ የአኩሪ አተር ልማቱን አስፋፍተው ለመቀጠል ፍላጎት አላቸው፡፡

አምራቾቹ ከግብርና ምርት ውል (ከኮንትራት እርሻ) በብዙ መንገድ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ድርጅቱ በቀጠራቸው የግብርና ባለሙያዎች ስለ አኩሪ አተርና ሱፍ ልማት በቂ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ ኬሚካልና የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን ድጋፍ ከድርጅቱ በጊዜ ስለሚያገኙ ሰብሎቹን በአግባቡ አልምተው በጥራትና በብዛት ማምረት ችለዋል፤ ያለምንም ደላላ ጣልቃገብነት ምርታቸውን ቀጥታ ለድርጅቱ ስለሚሸጡ ከገበያ ስጋት ነፃ ሆነዋል፡፡
እንዲሁም አኩሪ አተር የተጎዳውን አፈር በማዳበር ወደ ለምነቱ ስለሚመልስ አምራቾቹ አኩሪ አተር ለማልማት ያላቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው፡፡
የኮንትራት እርሻ አስመራቹ መንግስት ገብቶ ለመስራት የሚቸገርበት ቦታ ገብቶ በመስራት ለመንገስት አቅም ይፈጥራል፤ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ አምራቾች በቀላሉ እንዲስፋፉ፣ የአምራቾች የፋይናንስ እጥረት እንዲቀረፍ፣ የግብዓት አቅርቦት እንዲሳለጥ፣ አምራቹ ከገበያ ስጋት ነፃ እንዲሆን፣ እንዲሁም ምርታማነት እንዲጨምር የላቀ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡
በአጠቃላይ የግብርና ምርት ውል ለአምራች፣ ለአስመራችና ለሀገር ትልቅ ፋይዳ ስላለው ወደ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢወች እንዲስፋፋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
