ቦንጋ፣ ሚያዚያ 24/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) መንግስት የግብርና ምርት ጥራት፣ የአመራረት ቅልጥፍና እና ተወዳዳሪነት እንዲሁም የግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ ተመጋጋቢነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ እና የግብርና ምርቶች ገበያ ተኮር ምርቶችን ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ አዋጅ እና ደንቦች ተዘጋጅተው እየተሰሩባቸው ነው፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ከክልል ግብርና ቢሮ፣ ከንግድ ኢንቨስትመንት ቢሮና ከጀርመን የልማት ትብብር (GIZ-S2RAI) ጋር በመተባበር የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ባለሀብቱ በስፋት በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብለዋል፡፡


በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተሰሩት ስራዎች ከነበረው ዝቀተኛ የኢንቨስትመንት ፈሰት አሁን ላይ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከ527 በላይ መድረሳቸውን እና ከ177 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት ተረክበው እያለሙ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለሀብቶች የተረከቡትን መሬት በሙሉ አቅም በማልማትና ለአርሶ አደሩ ግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ እድል ለመፈጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ በበኩላቸው የግብርና ኢንቨስትመንት መንግስት በትኩረት ከሚሰራባቸው ንዑስ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ባለሀብቱን ለመደገፍና ምርታማነትን ለማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በተሻለ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርት ውል ውጤታማ እንዲሆን ባለሀብቶች ለገቡበት ውል ታማኝ ሆነው መስራት እንዳለባቸው መሪ ስራ አስፈጻሚው አሳስበው በዚህም ትላልቅ ካምፓኒዎች ወደ ዘርፉ በስፋት በማሰማራት ይበልጥ ውጤታማና ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት ተሰማርተው እያለሙ ሲሆን በዚህም በግብርና ምርት ውል ትስስር የተፈጠረለት ምርት 27.4 ሚሊዮን ኩንታል ታቅዶ ከእቅድ በላይ 37.2 ሚሊዮን ኩንታል ማሳካት ተችሏል፡፡
በመድረኩም በክልሉ ያለው የመልማት አቅም፣ ባለሀብቶችን እያጋጠማቸው ያሉ ተግዳሮቶችና በባለሀብቶች ዘንድ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሁም በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ከጀርመን የልማት ትብብር እና በሌሎች ተቋማት በዘርፉ ያሉ ተሞክሮዎች ላይ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ካሳሁን ማለቶ
ፎቶግራፈር፡-ጌታቸው ምትኩ
