የግብርና ምርታማነት፣ ፈጠራና ዘመናዊነት የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እውን ያደርጋሉ፡፡ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግና ለማዘመንም የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም፣ ውጤታማ የግብርና አሰራር ዘዴዎችን መተግበር፣ የኤክስቴንሽን ስርዓትን ማጠናከር፣ ሜካናይዜሽን፣ የግብዓት እና የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል በዋናነት የሚነሱ ናቸው፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከላት ለግብርና ምርታማነትና መዘመን ቁልፍ ሚና አላቸው። የግብርና ምርታማነት የሚረጋገጠው የምርምር ውጤቶች ከቤተ-ሙከራ አልፈው የአርሶአደሩ እና ኢንቨስተሩ ማሳ ሲደርሱ ነው። የዘርፉን ምርታማነት እያሳደጉ ካሉ የግብርና ምርምር ተቋማት መካከል የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነው፡፡
ማዕከሉ ከተመሰረተ 55 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በዋናነት በቡና ምርምር ላይ መሰረት አድርጎ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በሆርቲካልቸር፣ በእህልና ቅባት ሰብሎች ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማፍለቅና በማሰራጨት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ የግብርና አሰራሮችን እንዲሁም ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ረገድ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ማዕከሉ አገራችን ከቡና ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በምርምር የተገኙ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ በሽታን የሚቋቋሙ፣ የተሻለ ጣዕም ያላቸው እና ለየስነ-ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን በማፍለቅ ለቡና አብቃይ አካባቢዎች እያሰራጨ ሲሆን 51 የሚሆኑ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶአደሩና ኢንቨስተሩ ተደራሽ ማድረጉን የማዕከሉ ዳይሬክተር ለሚ ቤክሲሳ ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በዋናነት የአነስተኛ ይዞታ አርሶአደሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ ቢሆንም በዘርፉ እያደገ የመጣውን ኢንቨስትመንት በመደገፍ የግል ባለሃብቱ በምርምር ማዕከሉ የወጡ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዝርያዎችን የመጠቀም ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡
የእኛ ተልዕኮ ምርምር ማድረግ ብቻ ሳይሆን በምርምር የተረጋገጡ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ወደ አርሶ አደሮችና ኢንቨስተሮች ማድረስ ነው ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር፣ የተሻሻሉ የቡናና ሌሎች የሰብል ዓይነቶችን እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በተግባር ወደ ማሳ ማውረዱን ገልፀዋል።

“አገራችን ቡናን መጠቀም በሚገባት ልክ አልተጠቀመችም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን እንደ ሀገር የቡና ምርታማነትና ጥራት እየጨመረ በመምጣቱ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው” ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር፣ ለዚህ ውጤት ማዕከሉ ያወጣቸውና የተገበራቸው የምርምር ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ትልቅ ድርሻ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
የምርምር ማዕከሉ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር መሰረት በማድረግ የተለያዩ ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት አንዱ ከአንዱ በመማር ቴክኖሎጂው በልምድ ልውውጥ ወደ አርሶአደሩ እንዲወርድ ከማድረግ ባለፈ የግል ባለሃብቱ የምርምር ቴክኖሎጂው ዋነኛ ተጠቃሚ በመሆኑ ምርምሩን ይበልጥ ለማሳደግ የትብብር ስራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

በጅማና አጎራባች ዞኖች የሚገኙ በተለይም በቡና እና አኩሪ አተር ልማት ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች በዋናነት ምርምር ማዕከሉ የለቀቃቸውን አዳዲስ ዝርያዎችን መጠቀም መቻላቸው ምርታማነታቸውን በምርምሩ ሰርቶ ማሳያው ልክ ማድረስ ችለዋል፡፡
ቡናን በመስኖ ቴክኖሎጂ በማልማት ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚቻል በሰርቶ ማሳያዎች ኢንቨስተሩንና የአነስተኛ ይዞታ አርሶአደሩን በመስክ ማሳየት መቻሉን የታናገሩት አቶ ለሚ፣ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለመደው አሰራር መሄድ አዋጭ ባለመሆኑ የመስኖ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አሁን ያለውን የቡና ምርታማነት ማሻሻል ስለሚያስችል ለዚህ ደግሞ ኢንቨስተሩ ግንባር ቀደም ሆኖ መተግበር አለበት ብለዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ አሁን ካለበት በተሻለ ወቅቱ የሚጠይቀውን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ እንዲችልና ቴክኖሎጂውን አርሶአደሩና ባለሃብቱ በቀላሉ እንዲያገኙትና እንዲጠቀሙት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከምርምሩ የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች በማሳ ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ በትብብር መስራት ከተቻለ ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ይቻላል፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ማቲዎስ ተገኝ
