FDRE Ministry of Agriculture

አረንጓዴ አሻራ ለዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ!

በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት ይነገርላት የነበረችው ኢትዮጵያ በወቅቱ በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም ምክንያት የደን ሽፋናችን ወደ 3 በመቶ ወርዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መደህየት እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት እንደቆየ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ዓሉታዊ ተፅዕኖ በመከላከል የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲቻል የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅና በዘላቂነት መንከባብ አማራጭ የሌለው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ2011 ዓ.ም በክብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሀሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የተጀመረ ሲሆን ይህም ኢኒሼቲቭ የአካባቢን ተፈጥሯዊ ገፅታ ለመጠበቅና ለመንከባከብ በተለይም የደን መመናመንና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንዲሁም የሃገሪቱን የደንና የአረንጓዴ ሽፋን በማሳደግ ንፁህ አየርና ውሃ እንዲኖር በተጨማሪም ለበርካታ ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም የሃገራችን ክፍሎች የዝናብ ወቅትን ጠብቆ የመትከልና የመንከባከብ ስራዎች እየተከናወኑ ነዉ፡፡ በመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

በ2012 ዓ.ም 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን፣ በ2014 ዓ፣ም 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ 2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 8 ቢሊዮን ችግኝ የተተከለ ሲሆን በ2018 ዓ.ም 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል፡፡

በአጠቃላይ በአንደኛው እና በሁለተኛው ምዕራፍ የተተከሉ ችግኞችን 50 ቢሊዮን ለማድርስ ግብ የታጣለ ሲሆን ይህም ተግባር ሀገራችን በአለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሃ-ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም የደን ዛፍ ችግኝና ዘርፈ-ብዙ ጥቅም የሚሰጡ በአርሶ አደር ማሳ የሚተከሉ የጥምር ደን አካል የሆኑ የፍራፍሬ፣ የመኖና የማገዶ ዛፍ በተጨማሪም የከተማ ውበትን የሚያላብሱ ዛፎችን የመትከል ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

የፕሮግራሙ ውጤታማነት እና ስኬት የተገኘው ስራውን ሀገር አቀፍ በማድረግ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በችግኝ ተከላው በማሳተፍ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ካለው ትልቅ ሀገራዊ የልማት ፋይዳ ባሻገር አለም አቀፍ ትኩረት፣ አድናቆት እና ምስጋና ያገኘ ሲሆን ሌሎች ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ለሚያደርጉት ጥረት ፕሮግራሙን በሞዴልነት መከተል ጀምረዋል፡፡

በዚህም የጎረቤት ሀገራትን በአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ተሳታፊ በማድረግ በቀጠናው የበረሃማነት መስፋፋትን በጋራ መግታት እንዲቻል እየተደረገ ባለው ጥረት ለጂቡቲ መንግስት የተለያዩ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬና የዛፍ ችግኝ አቅርቦት እንደተደረገም ይታወሳል፡፡

በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ እና ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ያለው፣ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ እና አካባቢን በመልካም ጎኑ ተፅዕኖ የሚያሳድር ብሎም ሌሎች ሃገሮች ምድራችንን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ተግባር የሚያነሳሳ ኢኒሼቲቭ ነው፡፡

በቀጣይ ዓመታት የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የአረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግ በታቀደና በተቀናጀ መንገድ የፕሮግራሙ የልማት ስራዎች በልዩ ትኩረት ይተገበራሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች በመመርመር ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በትብብር ያዘጋጁት በብሔራዊ የግብርና ምርምር ስርዓት ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው የግብርና ሳይንስ ሴሚናር ተካሂዷል፡፡  

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት ባለፉት አመታት የምርምር ስርዓቷን በመገንባትና በማስፋፋት ረገድ በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

የውደፊቱ የኢትዮጵያ ግብርና የሚመራው በምርምር ላይ በሚደረገው ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በትብብር ስራ እውቀትን ወደ ተግባራዊ ለውጥ በመቀየር የተቀናጀ፣ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ፣ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ወደ አርሶና አርብቶአደሩ ማድረስ የሚያስችል የግብርና ምርምር ስርዓት መገንባት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ለመገንባት እና የገበያ ትስስር ማጠናከርን እውን ለማድረግ በውጤት ተኮር የሚመራ የምርምር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ውስጥ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችን በመፍጠር በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የውይይት መድረኩ እገዛው የጎላ መሆኑን ዶ/ር መለስ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የብሔራዊ የግብርና ምርምር ስርዓቶችን እንደገና መገንባት፣ ተቋማዊና ስትራቴጂካዊ ቅንጅት እና ለውጥ ፈጣሪ መንገዶች  በውይይቱ ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ

#Ethiopia#GreenLegacy#ForestDevelopment#NaturalResource