አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም/ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግብርና ምርምር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን የተበጣጠሰ አሰራር፣ ቅንጅታዊ ውስንነት እና የምርምር ውጤቶችን ወደ ተጨባጭ ለውጥ ማድረስ ያለመቻል የግብርና ምርምር ስርዓት ማነቆዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች በመመርመር ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በትብብር ያዘጋጁት በብሔራዊ የግብርና ምርምር ስርዓት ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው የግብርና ሳይንስ ሴሚናር ተካሂዷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት ባለፉት አመታት የምርምር ስርዓቷን በመገንባትና በማስፋፋት ረገድ በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

የውደፊቱ የኢትዮጵያ ግብርና የሚመራው በምርምር ላይ በሚደረገው ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በትብብር ስራ እውቀትን ወደ ተግባራዊ ለውጥ በመቀየር የተቀናጀ፣ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ፣ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ወደ አርሶና አርብቶአደሩ ማድረስ የሚያስችል የግብርና ምርምር ስርዓት መገንባት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ለመገንባት እና የገበያ ትስስር ማጠናከርን እውን ለማድረግ በውጤት ተኮር የሚመራ የምርምር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ውስጥ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችን በመፍጠር በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የውይይት መድረኩ እገዛው የጎላ መሆኑን ዶ/ር መለስ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የብሔራዊ የግብርና ምርምር ስርዓቶችን እንደገና መገንባት፣ ተቋማዊና ስትራቴጂካዊ ቅንጅት እና ለውጥ ፈጣሪ መንገዶች በውይይቱ ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
