FDRE Ministry of Agriculture

የግብርና አርበኞቻችን!


በዛሬው ዕለት የሚከበረውን 85ኛውን የአርበኞች መታሰቢያ ቀን ስናከብር የጀግኖች አያቶቻችንን ታሪክ እየዘከርን በእኛ ዘመን ታሪክ ለመስራት በመትጋት መሆን አለበት፡፡ በግብርናው ዘርፍ የልማት አርበኛ የሆኑ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች በዘርፉ ለተገኙት ስኬቶች ያበረከቱት አስተዋፅዖ የግብርና ልማት አርበኞች የሚያስብላቸው ነው፡፡


በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ70 ሺህ በላይ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች አሉ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገቡት ስኬቶችና የታሪክ እጥፋቶች መንግስት ለዘርፉ በቸረው ልዩ ትኩረት መሆኑ እሙን ነው፡፡


መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱም ባሻገር በዘርፉ ለተመዘገቡት ስኬቶች የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ከአርሶና አርብቶ አደሩ ጎን በመቆም ብዙ መስዋዕትነትና በገንዘብ የማይለካ ሙያዊ ዕውቀታቸውን እንዲሁም ውድ ህይወታቸውን ዋጋ በመክፈል ለስኬቱ እንደሻማ በርተው የቀለጡ ብዙዎች መኖራቸው የማይካድ ሃቅ ነው።


ለግብርናው ዘርፍ መዘመን እና ሽግግር በዘርፉ የተገኙትን ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል በቀበሌ ደረጃ ተመድበው ለአርሶና አርብቶ አደሩ የቅርብ ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማሳደግ ለዘርፉ ያላቸውን አበርክቶ ማላቅ ለነገ የማይተው ተግባር ነው፡፡


መንግስት ቀጣይነት ያለው የግብርና ዘርፍ ዕድገትን ለማረጋገጥ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊ ዕውቀት ለማስጨበጥ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ለሚገኙ ታታሪ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎቻችን የዕቀትና ክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በተመረጡ የግብርና ኮሌጆች ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።


የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ፣ ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንዲሁም የግብርናን ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እነዚህን ባለሙያዎች በእውቀትና ክህሎት ማሳደግ የመደመር መንግስት በትኩረት እየሰራበት የሚገኝ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡


በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የፖሊሲና ስትራቴጂ ዝግጅትና ትግበራ፣ ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራዎች፣ ዘመናዊ ግብርናን ዕውን ማድረግ፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ፣ ኩታ-ገጠም እርሻን በማስፋፋት ከፍጆታ ባለፈ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ዕድገትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ በርካታ ስራዎች ያለ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ከግብ ማድረስ ስለማይቻል ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የምትገኙ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ለምታደርጉት ጥረት ግብርና ሚኒስቴር ምስጋናውን ያቀርባል፡፡


በአጠቃላይ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የግብርናው ዘርፍ የልማት ስራዎች ላይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያዎች፤ እናንተ የዚህ ዘመን የግብርና ልማት አርበኞች ናችሁና ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ለግብርና ትራንስፎርሜሽን በተጨማሪም ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የበኩላችሁን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባችኋል፡፡