የግብርናውን ዘርፍ ለማሻገር በሚደረገው ርብርብ የግብርና ሜካናይዜሽን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
መንግስት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርቱን ለገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ አርሶአደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን እንዲያገኙ በማድረግ ለዘርፉም ዕድገት አበክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡

አርሶአደሮች በቁጠባና ብድር መልክ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸቱ በርካታ አርሶአደሮች እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት አሰጣጡ ከባህላዊ አሰራር ይልቅ በአንድ ሄክታር መሬት የሚገኘውን ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡
የአርሶአደሩን ድካም፣ ጊዜ እና የምርት ብክነት በመቀነስ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት የሚቻለው የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል መሆኑ እሙን ነው፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት በግብርናው ዘርፍ በሚወስዳቸው እርምጃዎች በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ሲሆን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለአብነት ይጠቀሳል፡፡
የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን እንዲገጣጥሙ፣ በሂደትም ወደ ማምረት እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን ፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍ አጋርነትን በማሳደግ፣ በሀገር ውስጥ ማምረትና መገጣጠምን በመደገፍ እና የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡
የኩታ ገጠም እርሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱም ለግብርና ሜካናይዜሽን መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በመደረጉ የአርሶአደሩ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም እያደገ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡
ለአብነትም በ2012 ዓ.ም 1 ሺህ 316 የነበረውን የትራክተር ቁጥር ወደ 27 ሺህ እንዲሁም የኮምባይነር ቁጥር ከ448 ወደ 8000 ማድረስ ተችሏል፡፡
አዘጋጅ፡- ዮሐንስ ደመቀ
