(አዲስ አበባ፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በሀገራችን በትምህርትና በምርምር ተቋማት የፈለቁ ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶች መደርደሪያ (Shelf) ላይ ተቀምጠው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ሲከስሙ ይስተዋላል።
በግለሰብ ደረጃ የሚሰሩ የፈጠራ ውጤቶችም በግለሰቡ የአቅም (በጀት) ውስንነት ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ ሳይሰራጩና ሳይተገበሩ ሃሳብ ብቻ ሆነው ይቀራሉ።

ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅና ማሻገር ባለመቻላችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት ብዙ ምንዛሬ እናወጣለን።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሀገር በቀል ዕወቀትን ለማጠናከር ክህሎት ኢትዮጵያ (Skill Ethiopia) ኢኒሼቲቭ ቀርጾ ፈጠራ ያላቸውን ግለሰቦች በማሰባሰብ ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራ ነው።

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩትም የግብርናና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ፣ የመተግበርና የማሻገር ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የመስኖ፣ የድህረ-ምርት፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ቀፎ፣ የአሲዳማ አፈር መከላከያ፣ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን… ሰርቷል።

በግብርናው ኢንቨስርመንት (በእንስሳት፣ በሆርቲካልቸር፣ በሰብል ምርቶችና በኮንትራት እርሻ ኢንቨስትመንት) የተሰማሩ የተለያዩ ባለሀብቶች ኢንስቲትዩቱ ያፈለቃቸውን ቴክኖሎጂዎች ጎብኝተዋል።
የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ እንደገለጹት የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሀገር በቀል የግብርና ቴክኖሎጆዎችን እያፈለቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የባለሀብቶችን የቴክኖሎጂ ክፍተት በመሙላት ረገድ ኢንስቲቱዩቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እበረከተ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ምን ዓይነት ቴክኖሎጂዎች እያመረተ መሆኑንና ባለሀብቶቹ የትኛውን ቴክኖሎጂ እንደሚፈልጉ በማስተዋወቅ ረገድ ጉብኝቱ ጉልህ ሚና አለው።

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ግብርናን ትራንስፎርም ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ሂደት ኢንስቲትዩቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክህሎት ኢትዮጵያ (Skill Ethiopia) አማካኝነት የግብርናና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶግራፈር፦ ጌታቸው ምትኩ
