ግብርናችንን ለማዘመን እንዲሁም ምርታማነትን ለማሳደግና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
መንግሥትም ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች በማቀናጀት የግብርናውን ዘርፍ ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ዘርፍ በማሸጋገር ላይ ይገኛል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የሚገኙት አቶ ፈቃዱ ነመራ ከቅጥር ሥራቸው በመውጣት በአሶሳ ዞን ዑራ ወረዳ ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት ገብተዋል።
15 የውሃ ገንዳዎችን በመገንባት ከ27 በላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እያለሙ ይገኛሉ።
እርሻቸው ከአትክልትና ፍራፍሬ እስከ የቅባት እህሎች፣ ከዓሳ እርባታ እስከ ወተትና ማር፣ ከቅመማ ቅመም እስከ ውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ያካተተ የተደራጀና የተቀናጀ የግብርና ማዕከል ሆኗል።
የተፈጥሮ ውበት፣ የውሃ አካላትና ምቹ የአየር ንብረትም እርሻውን ለመዝናኛና ለገጠር ቱሪዝም ምቹ እና ተመራጭ ስፍራ እያደረጉት ነው።
አቶ ፈቃዱ “በዛሬ ድካም ነገን ማረፍ፤ ለትውልድም መትረፍ” በሚል እሳቤ የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ምርት ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችንም በስፋት እያመረቱ ነው።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ8,904 በላይ ባለሀብቶች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው እያለሙ ይገኛሉ።
