ውድ የገፃችን ተከታታይ ቤተሰቦቻችን፡- በዛሬው የፕሮግራም እና ፕሮጀክቶች ዝርዝር ገላጭ ፅሁፋችን የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም/Rural Productive Safety-Net Program (RPSNP) ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ1997 ዓ.ም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የተጠቃሚ ቁጥር እና አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ አራት ምዕራፎችን አልፎ አምስተኛውንም ምዕራፍ እያገባደደ ይገኛል።
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በምግብ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከተረጅነት በማላቀቅ በዘላቂነት በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉና ጥሪት እንዲገነቡ ማድረግ ሲሆን ፕሮግራሙ የገጠር ነዋሪዎች በማህበረሰብ ስራ ላይ በመሳተፍ የወል ጥሪት እንዲገነቡም አስችሏል፡፡ በተጨማሪም ጊዜያዊ የስራ ዕድልም ፈጥሯል።

ፕሮግራሙ በራሱ የሚተገበር ሳይሆን፤ ከመንግስት ተቋማት የልማት ዕቅዶች ጋር ተዋህዶ በወረዳ፣ በክልል እና በፌደራል ደረጃ የሚሰሩ የልማት ዕቅዶች አካል ነው፡፡ በዚህም በ10 ክልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር ውስጥ በ494 ወረዳዎች፣ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን እና ከ25 ሚሊዮን በላይ የሰብአዊ እለት ደራሽ ድጋፍ (Shock Response) ለሚያስፈልጋቸው ተጠቃሚዎች በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተደራሽ በማድረግ የድጋፍ ማዕቀፉን አስፍቷል።
የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሽፋኑን በማሳደግ የተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለአብነትም፡-
በገጠሩ የሀገራችን አካባቢ የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፤ በዚህም የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎችን ድርቅ ከሚያስከትለው ጉዳት የመከላከል ስራ አከናውኗል፤

የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና ውሀ የማሰባሰብ ስራዎች በመስራት፤ የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ እንዲሁም ለልማት ስራ እንዲውሉ በማድረግ ተጠቃሚዎችን አደጋን የመቋቋም አቅማቸው እንዲጎለብት በማድረግ አጠቃላይ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አርንጓዴ አኮኖሚ የመገንባት ሂደት ላይ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
የሰው ጉልበትን በስፋት በመጠቀም በሚሰሩት የማህበረሰብ የልማት ስራዎች በገጠር በሚካሄደው የመሰረተ ልማት ግንባታ የገጠር ትናንሽ ከተሞች በቀላሉ እንዲገናኙ ከማድረጉም ባሻገር ህዝቡም የተሰሩለትን መንገዶች በመጠቀም ምርቱን ለገበያ በማቅረቡ ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከገበያ የሚፈልጋቸውን ግብዓቶችንና አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሏቸዋል፤
የእናቶችና ህፃናት አመጋገብ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን እንዲይዝ የሚያስችል አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህንንም በማድረግ በቤተሰብ ውስጥ ስርዓተ-ምግብ ሁኔታ እንዲሻሻል ተደርጓል፤
በተጨማሪም በማህበረሰብ ስራ ተሳትፎ በሚገነቡት የጤና ኬላዎችና የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታዎች የአካባቢው ህብረተሰብ የተሻለ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ፕሮግራሙ ባሳለፋቸው የትግበራ አመታት ውስጥ በወቅቱ ባለው ሀብት ተወስኖ በየምዕራፉ በብዙ ሚለዮን የሚቆጠሩ ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ተጠቃሚዎች በማሳተፍ የምግብ ክፍተታቸውን በመሙላት የግል ጥሪታቸውን በመጠበቅና ንብረታቸውን እንዳይሸጡ ከማድረጉም በላይ ለድህነት ቅነሳ ቁልፍ አስተዋፀኦ ሲያበረክት ቆይቷል።

በዚህም ሀገራዊ የድህነት መጠንን በ2 በመቶ በመቀነስ አስትዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የፕሮግራሙ አቀራረፅና የአተገባበር መርሆዎቹ የተጠቃሚ ቤተሰቦችን የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ እገዛ አድርጓል፡፡
ፕሮግራሙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ5.1 ሚሊዮን በላይ የፕሮግራም ተጠቃሚዎች በምግብ እራሳቸውን ችለው ተመርቀዋል፡፡ በተጨማሪም በአምስተኛው ምዕራፍ 4.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ኑሯቸው ተሻሽሎ ከፕሮግራሙ እንዲወጡና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ የተደረገ ሲሆን ባለፉት ምዕራፎች ከተደረጉ ጥረቶች ጋር በድምሩ 9.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏል፡፡
የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በስድስተኛው ምዕራፍ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ ስራዎችን በማካተት በሀገሪቱ ከተጀመሩት ዋና ዋና ፕሮግራሞች ጋር በመቀናጀት ማለትም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ አረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋት ጋር ትስስር በመፍጠር የማህበረሰቡ የላቀ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝና ይህንኑ የሚያስቀጥል ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከብሔራዊ ፖሊሲዎች ጋር ትስስር ያለው ሲሆን የፕሮግራሙ ምዕራፍ 6 (PSNP 6) ከኢትዮጵያ ሰፊ የፖሊሲ ምኅዳር ጋር በግልጽ የተቆራኘ ነው።
የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ፡- የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የምግብ ዋስትና ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ መሣሪያ ነው።
የአየር ንብረትን የመቋቋም ስትራቴጂ፡- ከ 2009 ጀምሮ ፕሮግራሙ የአየር ንብረት ለውጥን የመላማድና አሉታዊ ተጽእኖዎቹን ለመቀነስ ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢን ጉዳዮች ከማህበረሰብ ስራዎች ጋር በማዋሃድ እና ከፍተኛ የአየር ንብረት ስጋት ያለባቸውን ወረዳዎች ኢላማ አድርጓል።
የሰው ሃብት ልማት፡- የፕሮግረሙ ምዕራፍ 5 እና 6 በግልጽ ዓላማቸው የተመጣጠነ ምግብን፣ የጤና እና የትምህርት ውጤቶችን ለማሻሻል፣ በተጠቃሚዎች የጉልበት ተሳትፎ የሚሰሩ የማህበረሰብ ስራዎች የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማዕከል እንዲያደርጉ ያስችላል።
የአደጋ ስጋት አስተዳደር፡- የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከመንግስት የአደጋ ስጋት አስተዳደር ስርዓት ጋር የተዋሃደ ሲሆን ይህም ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥ ሚዛን እንዲኖር ያስችላል።
ብሔራዊ የስነ-ምግብ ፕሮግራም (NNP)፡- ፕሮግራሙ የምግብ እጥረትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ የስርዓት ምግብ ማሻሻያ ዘርፈ-ብዙ ኢኒሼቲቮች ጋር ተቀናጅቷል። በተለይም ከሰቆጣታ ዲክላሬሽን ጋር የተያያዘ ሲሆን የ15 አመት ተነሳሽነት (2016-2030) በተለይ ከሁለት አመት በታች ላሉ ህጻናት መቀንጨርን መቀነስን ለማስቆም/ለማሻሻል አስተዋጽኦ በሚያደርግ መልኩ የተዘጋጀ ነው።

በ6ኛው ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የፕሮግራም ድዛይን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች፡- የዓለም ባንክ በ200 ሚሊዮን ዶላር ክሬዲት ምዕራፍ ስድስትን በመጋቢት 2026 አጽድቋል። ቁልፍ ፈጠራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
ሥራ መፍጠር፡- ለ700,000 ሰዎች በክህሎት ስልጠና፣ በማማከርና ክትትል ድጋፍ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ጥሪት መፍጠሪ የገንዘብ ድጋፍ (grant support) በቤተሰብ ደረጃ ገቢ የሚያስገኙ ትንንሽ ንግዶችን/ኢንተርፕራይዞችን እንዲጀምሩ ወይም እንዲያሳድጉ ድጋፍ ማድረግ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ የማህበረሰብ ስራዎች፡- ለ6 ሚሊዮን ሰዎች የአጭር ጊዜ የስራ ስምሪት በተፋሰስ መልሶ ማቋቋም፣ በመሬት ማገገሚያ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሠረተ ልማት።
የሰው ካፒታል ትኩረት፡- የተመጣጠነ ምግብ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን በማስፋፋት የእጻናትን መቀንጨር መቀነስ እና የህጣናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዝግጅትና እድገት ማሻሻል።

የሴቶች እና ወጣቶች ማካተት፡- ለሴቶች ህብረት ስራ ማህበራት እና ለወጣቶች ስራ ፈጣሪነት የታለመ ድጋፍ።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ግልጽ የአሰራር ስርዓት፡ የተሻሻለ የቅሬታ ማስተናገጃ ዘዴዎች እና ተጠያቂነትን ለማጎልበት የሚያስችል የክትትል ሥርዓት ናቸው፡፡
#ከማምረትበላይ
#BeyondProduction
