ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግርን በቤተሰብና በሃገር ደረጃ በዘላቂነት ለመፍታት ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ከሚተገበርባቸው ክልሎች የትግራይ ክልል አንዱ ነው፡፡
በትግራይ ክልል ታህታይ ማጨው ወረዳ ናይ አጽሚ ቀበሌ እና በአድዋ ወረዳ ማሪያም ሸዊቶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ከእንስሳት መኖ ልማት እና ከእንስሳት እርባታ ስራዎች ጎን ለጎን ውሃን በማቀብ በመስኖ ልማት ስራ የሰብል ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡

በቀበሌዎቹ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በስፋት በመሰራታቸው የምንጭም ሆነ የጉድጓድ ውሃ ከመጎልበቱ ባሻገር የአፈር ለምነት በመጨመሩ ቀደም ሲል ምርት የማይሰጥ መሬት ምርት እንዲሰጥ ማድረግ ተችሏል፡፡
ለፕሮግራሙ ተጠቃሚ አርሶአደሮች በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዘዴ በኩል አስፈላጊው እገዛ የተደረገላቸው ሲሆን ተጠቃሚዎቹ ከግብርና ውጪ በሆኑ የገቢ ማስገኛ ስራዎችም ላይ በመሳተፍ ኑሯቸውን እያሻሻሉ ይገኛሉ፡፡
ሙሉውን ፅሑፍ ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
ፕሮግራሙ ለድህነት ቅነሳ ቁልፍ ለሆነው ለሰብል እና እንስሳት ልማት ዕድገት የራሱን አስተዋፅዖ ያበረከተ ስለመሆኑ ባለፉት አመታት የታዩ መልካም ተሞክሮዎችና ውጤቶች ማሳያ ናቸው፡፡
በክልሉ ሥር ለሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡና በገጠር ለሚኖሩ ሕዝቦች በዘላቂነት ከተረጂነት ወጥተው አምራች በመሆን እራሳቸውን በምግብ እንዲችሉ በማድረግ ረገድ የፕሮግራሙ አስተዋፀኦ የጎላ መሆኑን ከትግራይ ክልል የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የፕግራሙ አላማዎችን ሙሉ በሙሉ በክልሉ ማሳካት ተችሏል፡፡ በዋናነት የተራቆቱና ገላጣ የነበሩ አካባቢዎችን በመከለል እንዲያገግሙ በማድረግ የደን ልማቱን ከማሳደግ ባሻገር በታችኛው የተፋሰሱ ክፍል ተጠቃሚዎች የልማት ስረዎችን መስራት ችለዋል፡፡ ለክልሉ ምርትና ምርታማነት መጨመርም አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
ወ/ሮ ሙሉ በየነ በታህታይ ወረዳ የናይ አጽሚ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሙሉ የጥሪት መፍጠሪያ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ይህን ገንዘብ በመጠቀም ለመስኖ ስራ የሚያግዛቸውን የውሃ ፓምፕ ገዝተዋል ፡፡ እናት ፍየሎችንም በማርባት ህይወታቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ፡፡

በቀጣይ ወደ መደበኛ የብድር ስርዓት በመግባት በግብርናና ከግብርና ውጭ ባሉ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ገቢያቸውን የማሳዳግ እቅድ አላቸው፡፡ የ7 ልጆች እናትና ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ ታታሪ እናት ናቸው፡፡
ወ/ሮ ትንሳኤ ገ/ማሪያም ደግሞ በአድዋ ወረዳ የማሪያም ሸዊቶ ቀበሌ ነዋሪና የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ተጣቃሚ ሲሆኑ በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፍተው ባገኙት ትርፍ በግ ገዝተው በማርባት ተጨማሪ ገቢ በመፍጠር ይተዳደራሉ፡፡

የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በሚል መንግስት ያስቀመጠውን የልማት አቅጣጫ ተከትሎ በፕሮግራሙ እገዛ እራሳቸውን የቻሉ ተጠቃሚዎችን በማስመረቅ የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

