አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የምዕራፍ 5 ማጠቃለያ መርሀ-ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የአፍሪካ ትልቁ ማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም እና የምግብ ዋስትናን፣ የአካባቢ መልሶ ማቋቋምን እና የላቀ የኑሮ ልማትን በማገናኘት ረገድ በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ ፕሮግራሞች አንዱ ነው።
ፕሮግራሙ ዜጎችን ከተረጂነት በማላቀቅ ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ በማገዝ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው ተጠቃሚዎች የኑሮ ሁኔታቸው እንዲሻሻል፣ የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ፣ የገበያ ትስስር እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነው ሀብት እንዲያፈሩ እና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለአካታች የዘላቂ ልማት ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በመድረኩም የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ምዕራፍ 5 ማጠቃለያ ላይ ያተኮረ ዕሁፍ ቀርቦ ፓናል ውይይት ከተካሄደ በኃላ በፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የተመረቱ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን የሚያሳዩ አውደ-ርዕይ ጉብኝት ተደርጓል፡፡

