በሀገራችን ምስራቃዊ ክፍል በአርብቶአደር አካባቢዎች ላይ የሚተገበረው የድርቅ መቋቋሚያ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት በአፋር ዝቅተኛ ቦታዎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮችን የድርቅ መቋቋም አቅምና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል የሚሰራ ነው፡፡

የፕሮጀክቱም ዋና ዋና ተግባራት የመጀመሪያው የውሃ መሠረተ-ልማትን ማስፋፋት ሲሆን በዚህም፤ የውሃ ማጠራቀሚያ አማራጮችን ማልማት፣ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት መገንባት እንዲሁም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ጥልቅ ጉድጓዶችን ለመጠጥ ውሃ ወይም ለመስኖ አገልግሎት እንዲሰጡ ማልማት ነው።
ሁለተኛው የግጦሽ መሬት መልሶ ማቋቋም ሲሆን የክልላዊ የፕሮሶፒስ መስፋፋት መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና መተግበር፣ ዘላቂ የግጦሽ መሬት አያያዝ ልምዶችን መተግበር፣ ክልላዊ የዘር አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት እና በማሽነሪ የታገዘ የፕሮሶፒስ ምንጠራና የግጦሽ መሬት መልሶ መዝራት ስራዎችን ማስፋፋት ነው።
ሶስተኛው የፕሮጀክቱ ዋና ተግባር የጥገናና ኦፕሬሽን ድጋፍ ሲሆን ለግጦሽ መሬት መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆኑ ማሽነሪዎችና መሳሪያዎች የጥገና እና ኦፕሬሽን ክፍል ማቋቋም ሲሆን አራተኛው ዋና ተግባር ደግሞ ማህበራዊ መሠረተ-ልማት ግንባታ ሲሆን በዚህም የማህበራዊ መሠረተ-ልማቶችን ዲዛይን መከለስና ማዘጋጀት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

የጀርመን መንግስት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት በጀርመን ልማት ባንክ በኩል ድጋፍ የተደረገለት ይህ ፕሮጀክት ጠቅላላ ግምቱ 17 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ከጀርመን መንግስት በተገኘ 15 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
የፕሮጀክቱ የበጀት ክፍፍል በዋናነት በውሃ መሠረተ-ልማት እና ተፈጥሮ-ተኮር መፍትሄዎች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት 6.85 ሚሊዮን ዩሮ፣ የግጦሽ መሬት መልሶ ማቋቋምና አያያዝ 3.52 ሚሊዮን ዩሮ፣ ለመሠረተ-ልማት እና ለማሽነሪዎች ጥገና እና ኦፕሬሽን ድጋፍ 0.45 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም በመሠረታዊ የማህበራዊ መሠረተ-ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት 0.08 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
የድርቅ መቋቋሚያ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት እ.አ.አ በሴፕቴምበር ወር 2021 ተፈርሞ በግንቦት 2023 ወደ ተግባር የገባ ሲሆን እስከ ሚያዝያ 2027 ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
ፕሮጀክቱ በግብርና ሚኒስቴር እና በክልል ደረጃ በአፋር ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አማካኝነት የተቀናጀ አመራር በመስጠት እየተተገበረ ይገኛል።

